በስዊድን የአውሮፓ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች በተሰበሰቡበት ሠላማዊ ሰልፍ ተደረገ
ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እንድትፈታ ተጠየቀ

በማትያስ ከተማ
Ethiopia Zare (ሰኞ ጳጉሜን 2 ቀን 2001 ዓ.ም. September 7, 2009)፦ ባለፈው ቅዳሜ ነሐሴ 30 ቀን 2001 ዓ.ም. (September 5, 2009) ”ሼፕስሆልመን” በሚባለውና በስቶኮልም ግራንድ ሆቴል አጠገብ በሚገኝ የስብሰባ ቦታ የአውሮፓ የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች ሰብሰባ ተጀምሯል። በስቶክሆልምና አካባቢው የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን በስፍራው በመገኘት ሠላማዊ ሰልፍ ከማድረጋቸውም በላይ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ካለምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ትፈታ ዘንድ መልዕክታቸውን ለተሰብሳቢዎቹ አሰምተዋል።
ቅዳሜ ዕለት የስዊድን የአንድነት ፓርቲ የድጋፍ ማኅበር ያስተባበረው የተቃውሞ ሰልፍ ሚንስትሮቹ በሚያልፉበት በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት አካባቢ ተካሂዷል። ሰልፈኛው በሀገራችን ያለውን የአገዛዝ ሥርዓት በመቃወም የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ እና ሌሎችም የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጠይቋል።

በቦታው ላይ የስዊድን የሶሻል ዲሞክራት የፓርላማና የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ አባል የሆኑት ወ/ሮ ካሪና ሄግ በመገኘት ንግግር አድርግርዋል። ”... ኢትዮጵያውያን በስፖርትና ስማችሁን ሊያስጠራ በሚችል ሁሉ ቅድሚያ ቦታ ያላችሁ በመሆኑ ልትኮሩ ይገባችኋል። ባሁኑ ጊዜ የደረሰባችሁንም ችግር በጋራ መወጣት አለባችሁ። ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ሳትፈታ ምርጫ የሚባል ነገር የሚሞከር አይሆንም ..” በሚለው ጠንካራ መልዕክት በያዘው ገለጻቸው መሃል፤ ብርቱካን የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚያደርሰው በደል ምልክት እንደሆነችም ገልጸዋል።
ከዚህ በመቀጠል ለተሰብሳቢዎቹ ለውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች የተጻፈውን ደብዳቤ የድጋፍ ማኅበሩ ሰብሳቢ በሆኑት በአቶ ራስወርቅ መንገሻ የተመሩ መልዕክተኞች ለፕሬስ መምሪያው ኃላፊ አንደርሽ የርሊ አስረክበዋል። ኃላፊውም ደብዳቤውን ለስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ለካርል ቢል እንደሚያቀርቡ አስታውቀዋል። (የደብዳቤውን ሙሉ ቃል እዚህ በመጫን ያንብቡ!)
በመጨረሻም ”በደል ይረሳል ወይ?” የሚል ግጥም ቀርቦ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ከጠዋቱ 5:00 ሰዓት (11:00 ሰዓት) የተጀመረው ሰልፍ በ6:45 (12:45) ሰዓት ተጠናቋል።



