ከጳጉሜን 3 ጀምሮ በኦሮሚያ ከ400 በላይ ሰዎች ታስረዋል

Ethiopia Zare (እሁድ መስከረም 10 ቀን 2002 ዓ.ም. September 20, 2009)፦ በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ የሚኖሩ የ8ኛ እና የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች "የኦህዲድ አባልነት መታወቂያ ካላመጣችሁ ለሁለተኛ ደረጃ እና ለመሰናዶ ትምህርት አትመዘገቡም" መባላቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።

 

ተማሪዎቹ በኦህዲድ ካድሬዎች ከፍተኛ ማስፈራራት የሚደርስባቸው ሲሆን፣ ትምህርታቸውን ለመቀጠል የኦህዲድ አባል ሆነው መመዝገብ ብቸኛ አማራጫቸው እንደሆነ ተነግሯቸዋል።

 

ዓርብ መስከረም 8 ቀን 2002 ዓ.ም.፤ የኦሮሞ ህዝብ ኮንግረስ (ኦህኮ) እና የኦሮሞ ፌደራሊስት ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኦፌዲን) በጋራ ሆነው ባወጡት መግለጫ በአካባቢው እስራት፣ ማስፈራራትና ወከባ መበራከቱን ገልጸው፤ በቅርቡ እንዳረጋገጡት ቁጥራቸው ከ412 የሚበልጡ የድርጀቶቹ አባላትና ደጋፊዎች ከጳጉሜን 3 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምሮ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ተይዘው ታስረዋል።

 

ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ዛቻ ተሰንዝሮባቸዋል፣ ለማስፈራሪያ እንዲሆን ተብሎ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ፎቷቸው እንዲቀመጥ፣ ስምና ፊርማቸው በግዳጅ እንዲሠፍር ተደርጓል። መግለጫውን ያወጡት ሁለቱ ፓርቲዎች ይሄን የመሰለውንና በምርጫ 2002 የመሳተፍን ተስፋ የሚያደበዝዝ ድርጊት በአስቸኳይ እንዲያስቆም ገዥውን ፓርቲ በመግለጫቸው ጠይቀዋል።

 

የኢህአዲግና የኢትዮጵያ መንግሥት ፖለቲካ ተቀናቃኝ የሆኑት እና በዶክተር መረራ ጉዲና እና በአቶ ቡልቻ ደመቅሳ የሚመሩት ፓርቲዎች በአንድነት ባወጡት የጽሑፍ መግለጫ ላይ፤ በምዕራብ ሸዋ ዞን 222 ሰዎች፣ በሰሜን ሸዋ 12፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ 9፣ ምስራቅ ወለጋ ዞን 46፣ ምእራብ ወለጋ ዞን 33፣ ጅማ ዞን 3፣ በአርሲ ዞን 17 በቦረና ዞን 16፣ በጉጅ ዞን 13፣ ፊንፊኔ ዙሪያ 8 ሰዎች፣ ምዕ/አርሲ 4፣ ምስ/ሐረርጌ 2፣ ምስ/ሸዋ 7፣ ሆ/ጉ/ወለጋ 18፣ አዲስ አበባ 2 በጠቅላላ ካሳለፍነው ዓመት መገባደጃ ጀምሮ 412 አባላቶቻቸው ለእስር መዳረጋቸውን ገልጸዋል። (ሙሉውን መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ