ቸርቻሪ ነጋዴዎች ቫት እንዲሰበስቡ ተጠየቀ
Ethiopia Zare (እሁድ መስከረም 24 ቀን 2002 ዓ.ም. October 4, 2009)፦ ካፒታላቸው ከ10ሺ ብር የማይበልጥ የንግዱ ማኅበረሰብ ቫት ከፋይ ካልሆናችሁ ክሊራንስ አይሰጣችሁም መባላቸውን አንዳንድ ነጋዴዎች ለኢትዮጵያ ዛሬ ገለጹ።
በችርቻሮ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች እንደገለጹት “አለባችሁ የተባልነውን ታክስ በሙሉ ከፍለን ንግድ ፍቃድ እንዲታደስልን ንግድ ሚኒስቴር ስንሄድ ቫት ሰብሳቢ መሆን አለባችሁ፤ አለበለዚያ ፈቃዳችሁ አይታደስላችሁም ተብለናል" ሲሉ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገለጹ። ቫት ከ500 ሺህ ብር በላይ በዓመት ለሚያስገቡ አገልግሎት ሰጭዎች እንጂ ለአነስተኛ ንግድ ላይ ለተሰማሩ እንደማይሰራ ይታወቃል።
አቶ አህመድ የተባሉ ነጋዴ “መንግሥት ነጋዴዎችን ለምንድነው እንደጠላት እያየ የሚጠራጠረው? ነጋዴው የቀን ገቢውን ሲናገር፣ ገማቾች ሦስት እጥፍ ደምረውበት ይሄዳሉ፤ የሥራውን ፀባይ ሳያውቁ የመሰላቸውን እያደረጉ ነው። በዚያ ክርክራችንን ሳንጨርስ አሁን ደግሞ ቫት ተመዝገቡ የምንባለው ምን እንድንሆን ተፈልጐ ነው? ህዝቡ ሁሉ አብዶ ጨርቁን ጥሎ ጐዳና ላይ ቢለፈልፍ መንግሥት የሚያገኘው ጥቅም ምንድነው?” በማለት ምሬታቸውን ገልጸዋል።
አቶ ስንታየሁ ደምሴ የተባሉ በችርቻሮ የንግድ ዘርፍ የተሰማሩ ግለሰብ በበኩላቸው፤ “ምርጫ ሊደርስ ሲል እንደነዚህ ዓይነት ነገሮች መንግሥት ማድረግ ይወዳል። በ1997 ምርጫ ዋዜማ በተመሳሳይ ወር በታክስ እዳ ውዥንብር ውስጥ እንድንገባ፣ ከመንግሥት ጋር እንድንቆራረጥ ከሆንን በኋላ ምሬያችኋለሁ ተባልን። አሁንም ደግሞ አንዴ በአሻራ እያስፈሩና ያለገቢያችን ቫት እንድንከፍል እየጠየቁን ነው። በቫት ክፍያ ምክንያት የሚጐዳው ኅብረተሰቡ ነው። ኀብረተሰቡ አልገዛም ካለ እኛም ድርጅታችንን ዘግተን የረሃብተኛውን ቁጥር ከፍ እንዲል እናደርገዋለን። መንግሥት ይሄን ከፈለገ ጊዜው ሩቅ አይደለም” ብለዋል።
በሕጉ መሠረት ቫት ተመዝጋቢ የሚባሉት የቀን ገቢያቸው ሁለት ሺህና ከዚያ በላይ የሆኑ ሲሆን፣ አሁን ግን በቀን ከመቶ ብር በታች ገቢ ያላቸው በመሉ ቫት ሰብሳቢ እንዲሆኑ መመሪያዎች እየወጡ መሆኑ ታውቋል።



