ት/ቤቶች ከምርጫው በፊት ይዘጋሉ

Ethiopia Zare (እሁድ መስከረም 24 ቀን 2002 ዓ.ም. October 4, 2009)፦ ክረምቱን ሥልጠና ሲያደርጉ የሰነበቱ መምህራን ከሥልጠና በኋላ የገዥው ፓርቲ የአባልነት ፎርም እንዲሞሉ መጠየቃቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።

 

በሥልጠናው ሂደት የተሳተፉ መምህራን እንደገለጹት፤ በተለያዩ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መርሆዎች ሥልጠና ከተሰጣቸው በኋላ የኢህአዲግ አባል እንዲሆኑና ፎርም እንዲሞሉ መጠየቃቸውን በመቃወማቸው ከሥልጠና ሰጭ ካድሬዎች ጋር መወዛገባቸውን ለማወቅ ችለናል።

 

በአብዮታዊ ዲሞክራሲና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ በዞን ተከፋፍሎ ሲሰጥ የሰነበተው ሥልጠና ላይ የተሳተፉ መምህራን "ሥራችንን ከምናጣ ፎርሙን ብንሞላ ይሻላል" ያሉ ሰዎች በአንድ ወገን፤ "የለም እኛ በሙያችን ነው መጠራት ያለብን እንጂ፤ በአባልነት ተመዝግበን በየጊዜው በስብሰባና በግምገማ ሥራችንን መበደል የለብንም" በሚል ክርክር ገጥመው እንደነበር ለመረዳት ችለናል።

 

በመጨረሻም ሥጋት ያየለባቸው ፎርሙን ሲሞሉ፤ ሌሎች በበሽታና በጡረታ አማካኝነት የአባልነት ፎርሙን ሳይሞሉ መቅረታቸው ታውቋል።

 

ከመምህራን ውጭ ሌሎች መስሪያ ቤቶችም ክረምቱን በሙሉ በተመሳሳይ ሥልጠና ላይ መቆየታቸው የሚታወቅ ሲሆን፤ በተያያዘም የዘንድሮው የትምህርት ዘመን ግንቦት ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው ምርጫ ጋር በተያያዘ ቀደም ተብሎ እንዲጠናቀቅ በየትምህርት ቤቶች ትዕዛዝ ተላልፏል። ዩኒቨርስቲዎችና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በሚያዝያ ወር ትምህርታቸውን እንደሚያጠናቅቁና የሚመረቁ ተማሪዎችም ምረቃ ሥነሥርዓታቸው በዚሁ ወር እንደሚሆን ታውቋል።

 

በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ ተማሪዎች ባነሱት ጥያቄ የ10 ዓመት ሕፃን ልጅን ጨምሮ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፉ ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ