የቀድሞ ጋዜጦችና መጽሔቶች ስም ሊከፋፈል ነው
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ጥቅምት 7 ቀን 2002 ዓ.ም. October 17, 2009)፦ ከ1984 ወዲህ ሥራ ጀምረው በተለያዩ ምክንያቶች ሥራቸውን ያቆሙ የጋዜጣና መጽሔት ስያሜዎች ከባለቤቶቻቸው ውጭ ለሌሎች ሊከፋፈሉ እንደሆነ ተጠቆመ።
በኪሳራም ሆነ በተለያዩ አስገዳጅ ምክንያቶች ከገበያ የወጡት ጋዜጦችና መጽሔቶች ካሁን በፊት ለሌሎች መስጠት ተከልክሎ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ለጠያቂዎች ይሰጣል።
በመንግሥት እገዳ የተጣለባቸው፣ በፍርድ ቤት የታገዱ ጋዜጣና መጽሔቶችን እንደማይመለከት የገለጹት ምንጮቻችን ስያሜውን ለመውሰድ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ለቀድሞ ባለቤታቸው ሲሆን፤ ባለቤቶቹ ካልፈለጉ ግን ለሌሎች የሚፈልጉ ሰዎች ይሰጣል ተብሏል።
ጋዜጦቹና መጽሔቶች ስማቸው እንጂ ይዘታቸው የህዝብ ወገን ሆነው ሊወጡ አይችሉም የሚሉ አስተያየት ሰጭዎቸ፤ ኅብረተሰቡን ጋዜጣውና መጽሔቱ ቀድሞ በነበረው ስምና ዝና ለማታለል የታቀደ ይሆናል፤ ስድስት ወራት ያህል በቀረው የ2002 ምርጫ ኢህአዲግ በድብቅ ስፖንሰር የሚያደርጋቸው ጋዜጦች በቅርቡ ሊቋቋሙ እንደሚችሉና የህዝብ ወገን መስለው ለመቅረብ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርጉም ምንጮቻችን አክለው ገልጸዋል።



