ለተቃዋሚዎች የምርጫው መድረክ መጥበቡ ተገለጸ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ጥቅምት 7 ቀን 2002 ዓ.ም. October 17, 2009)፦ በኢትዮጵያ በምርጫ 2002 ሊኖር የሚችል የመንግሥት ተቃዋሚ ኃይሎች ተሳትፎ እንደሌለ የሀገሪቱ ፖለቲከኞች አስታወቁ።
ይህን ካስታወቁት ሰዎች መካከል አንዱ የቀድሞው ኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ናቸው። እኚሁ ፓለቲከኛ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል “ገዥው ፓርቲ ብቻውን ተወዳድሮ ብቻውን ማሸነፍ የሚፈልግ በመሆኑ የተቀናቃኞቹን የፖለቲካ መጫወቻ ሜዳ በሙሉ አጥሯል” ብለዋል። በቅርቡ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ወለጋ ደምቢዶሎ ተጉዘው ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ መጠርጠራቸውን ያስረዱት ዶክተሩ ከወረዳ ጀምሮ እስከ ጐጥና ብሎም እስከ መንደር የዘረጋው ህወሓት ኢህአዲጋዊ የካድሬዎች ቁጥጥር፤ የህዝቡን አማራጭ የፖለቲካ ድርጅትና አማራጭ ሀገራዊ ሀሳብ የመፈለግ ዝግጁነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባ መሆኑን ነው ግልጽ ያደረጉት።
እሳቸው ጨምረው እንዳሉት በወለጋና አካባቢው በምርጫ 97 ማግስት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ተከርችመዋል፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከማንኛውም የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ሰው ጋር ግንኙነት ያደረገ ዜጋ ወደ እስር ቤት ይወስዳል፣ በ2002 ምርጫ ኦህዴድ ኢሕአዴግን ወይም ገዥውን ፓርቲ ብቻ እንዲመርጥ ይገደዳል።
ይህ በወለጋ፣ ደምቢ ዶሎና ቄለም የተስተዋለው ሁኔታ በመላው ምዕራብ ሸዋ፣ በአርሲ እና በሌሎችም የኦሮሚያ ዞኖች ውስጥ በግልጽ እንደሚስተዋል የገለጹት ደግሞ ዶክተር መራራ ጉዲናና የእሳቸው ፓርቲ ዋንኛ አባል የሆኑ አቶ አልባና ሌሊሳ ናቸው። የኦሮሞ ፌደራሊስት ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሰዎችም ከፍ ሲል በዶክተር ነጋሶ ጊዳዳና በዶክተር መራራ ጉዲና በኩል የተገለጸውን ሀሳብ ይጋራሉ።
በምርጫው ለመሳተፍ መዘጋጀት በሀገር ቤት ላሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ምንም አይነት አማራጭ የሌለው ስልት ነው የሚሉ በምርጫ ሂደት ላይ ጥናት ያቀረቡ የፖለቲካ ተንታኝ ወያኔ/ኢህአዲግ ተቃዋሚዎች ተሰላችተውና ሜዳው ጠቧል ብለው ራሳቸውን ከምርጫ ውጭ እንዲያደርጉ ብዙ ጥረቶችን እንደሚያደርግና ያለተቀናቃኝ ብቻውን ለመሮጥ የሚያስችለውን ጥርጊያ አመቻችቶ ለታዛቢዎች በመፍቀድና ዲሞክራሲያዊ የሚስብሉ መስፈርቶችን በማሟላት በውጩ ማኅበረሰብ ዘንድ ለመጭው አምስት ዓመት የዲፕሎማት ሥራውን አጠናክሮ ለመግዛት የሚያስችለውን መንገድ ላለመክፈት ተቃዋሚዎች ቆም ብለው ማጤን እንደሚገባቸውና በምርጫው መሳተፋቸውን እስከመጨረሻው ማሳወቅ እንደሚገባቸው አስተያየታቸውን ችረዋል።



