ቃሌ የሻማ ማብራት በዲሲ ተካሄደ
Ethiopia Zare (ሰኞ ጥቅምት 16 ቀን 2002 ዓ.ም. October 26, 2009)፦ ትናንት እሁድ ጥቅምት 15 ቀን 2002 ዓ.ም. (ኦክቶበር 25 ቀን 2009) በዋሽንግተን ዲሲ በዋይት ሐውስ ፊት ለፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት ከምሽቱ 12 እስከ 2 ሰዓት ድረስ “ቃሌ” የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት መካሄዱን ከስፍራው ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የደረሰው ዘገባ ጠቆመ።
በአንድነት ፓርቲ የዲሲ ሜትሮ የድጋፍ ቻፕተር ያዘጋጀው ይኸው የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት የተጀመረው በሕሊና ፀሎት ነበር። የሕሊና ፀሎቱ በገዥው ፓርቲ በግፍ የተገደሉ ኢትዮጵያውያንን፣ በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ሰማዕት የሆኑትን፣ በረሃብ ለሞቱና በአሁኑ ሰዓት ስቃይ ላይ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ለአንድ ደቂቃ ታስበዋል።
በቃሌ የሻማ ማብራት ሥነሥርዓት ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን ለፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ የተለያዩ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። ከእነዚህም ውስጥ የኦባማ አስተዳደር ያለምንም ጥፋት በግፍ የታሰሩትን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳንና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲያደርግ፣ የኦባማ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ ለዲሞክራሲ የሚደረገውን ትግል እንዲደግፍ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ነፃነትና ዲሞክራሲ እንደሌለና ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተካሄደ እንዳለና የኦባማ መንግሥት ይህን እንዲያስቆም፣ … የሚሉ ይገኙበታል።
የዲሲ ሜትሮ ቻፕተር የቦርድ አባል የሆኑት አቶ ይልማ አዳሙ በሻማ ማብራት ሥነሥርዓቱ ላይ ንግግር አድርገዋል። አቶ ይልማ በዚሁ ንግግራቸው ላይ “ወ/ት ብርቱካን ያለምንም ጥፋት በግፍ መታሰሯን አይቶና ሰምቶ ዝም የሚል ኢትዮጵያዊ እንጂ፤ አሳሪዎቹ ሊገርሙን አይገባም” ብለዋል።
የቨርጂኒያ 46ኛው ዲስትሪክት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እጩ የሆኑት ዶ/ር ሳሻ ጎንግ በሻማ ማብራቱ ሥነሥርዓት ላይ በእንግድነት ተገኝተው የነበረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያውያኖች በኢትዮጵያ ዲሞክራሲን ለማስፈን የሚያደርጉትን ትግል እንደሚደግፉ ገልፀዋል።
የአንድነት ፓርቲ የዲሲ ሜትሮ የድጋፍ ቻፕተር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ አለማየሁ አበበ ባደረጉት የመዝጊያ ንግግር ላይ፤ በኢትዮጵያ የሚደረገው አፈናና ግድያ እየቀጠለ በመምጣቱ ትግሉ እንደሚቀጥል ገልጸዋል። በመጨረሻም የሻማ ማብራቱ ሥነሥርዓት ተካፋይ የሆኑትን በሙሉ በማመስገን፤ ወደፊትም ትግሉ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።



