የ2002 ዓ.ም.ቱ ምርጫ ግንቦት 15 ይካሄዳል
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2002 ዓ.ም. November 3, 2009)፦ በያዝነው የኢትዮጵያ 2002 ዓ.ም. የሚካሄደው ብሔራዊ ምርጫ በመላው ሀገሪቱ እሁድ ግንቦት 15 ቀን 2002 ዓ.ም. (ሜይ 23 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.) በመላው ኢትዮጵያ እንዲካሄድ ምርጫ ቦርድ ዛሬ አፀደቀ።
የደርግ ሥርዓት ከወደቀ በኋላ ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደው ይኸው ሀገር አቀፍ ብሔራዊ ምርጫ የድምፅ መስጫው ቀን ግንቦት 15 ቀን እንዲሆንና ከአንድ ወር በኋላ ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2002 ዓ.ም. (ጁን 21 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.)ደግሞ ውጤቱ የሚገለጽበት እንዲሆን በዛሬው ዕለት የምርጫ ቦርድ ማጽደቁን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዘገባ አስረዳ።
የድምፅ መስጫ ቀኑ በመላው ኢትዮጵያ በአንድ ቀን እንዲሆን (ግንቦት 15 ቀን 2002 ዓ.ም.) ምርጫ ቦርዱ አስፈላጊ ናቸው ያላቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ማጠናቀቁን የቦርዱ ሰብሳቢ ፕ/ር መርጋ በቃና መግለፃቸውን ለመረዳት ችለናል።
በዚህ የ2002 ምርጫ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ወገን ካለምንም ቅድመ ሁኔታ በምርጫው እንደሚሳተፍ የገለፀው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሲሆን፣ ይህንኑ የገለጹት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያለው ባሳለፍነው ሣምንት መገባደጃ ላይ ነው።
ባለፈው ሣምንት ጥቅምት 17 ቀን 2002 ዓ.ም. ከተቃዋሚዎች ወገን በኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል የሚመራው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ)፣ በአቶ አየለ ጫሚሶ የሚመራው ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ እና የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ከገዥው ፓርቲ ኢህአዲግ ጋር በመጭው ምርጫ የፓርቲዎች የሥነምግባር ደንብና የማስፈፀሚያ መመሪያ ሰነድ በትብብር ማፅደቃቸው ይታወቃል።
በሌላ በኩል ደግሞ ስምንት ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና ሁለት ታዋቂ ግለሰቦችን የያዘው መድረክ ለዲሞክራሲያዊ ምክክር በኢትዮጵያ (መድረክ) ውይይቱን ረግጦ መውጣቱን መዘገባችን አይዘነጋም።



