አምስት የሱማሌ ክልል የእስልምና ጉዳይ አመራሮች ታሰሩ
Ethiopia Zare (አርብ ኅዳር 11 ቀን 2002 ዓ.ም. November 20, 2009)፦ በሱማሌ ክልል የእስልምና ጉዳይ ጽ/ቤት ውስጥ ይሠሩ የነበሩ አምስት አመራሮች ከ15 ቀን በላይ መታሰራቸውን ምንጮች ገለጹ።
እንደምንጮቻችን ገለጻ የሱማሌ ክልል የእስልምና ጉዳይ ሊቀመንበር ም/ሊቀመንበርና ሌሎች የምክር ቤቱ አመራሮችም የታሰሩ ሲሆን የመታሰራቸው ምክንያት መንግሥትንና ዋናውን የእስልምና ጉዳይ አንታዘዝም በማለታቸው እንደሆነ ተገልጿል።
ከእስልምና ጉዳዮችና ከክልሉ መንግሥት የመጣላቸውን መመሪያ አንቀበልም ያሉት እነዚሁ አመራሮች “እኛ ሃይማኖታዊ ጉዳይ እንጂ ፖለቲካዊ ጉዳይ ለመሥራት አይደለም እዚህ የተቀመጥነው” ማለታቸው ታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ለአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ለሊቀመንበርነት ታጭተው የነበሩት አንጋፋው የኢስላም ምሁር ሐጂ በሽር ዳውድ ሥልጣኑን አልፈልግም ማለታቸው ከመገለጹም ሌላ ምሁሩ ሥልጣኑን ያልፈለጉት ምክንያት በ’ተጨማለቀ’ ባሉት አሠራር መሥራት ባለመፈለግ ሲሆን ም/ቤቱ ግን በጤና መታወክ ምክንያት አልፈልግም ብለዋል የሚል መልስ ሰጥቶ በምትካቸው ሌሎች ሰዎች እንዲቀመጡ አድርጓል።



