Ethiopia Zare (አርብ ኅዳር 11 ቀን 2002 ዓ.ም. November 20, 2009)፦ የዓለም የምግብ ሽልማት ተሸላሚ ለሆኑት ለፕሮፌሰር ገቢሳ እጅታ ከኦነግ የመግደል ሙከራ እንዳይደረግባቸው በልዩ የደህንነት አባላት ጥበቃ እንደሚደረግላቸው ምንጮቻችን ጠቆሙ።

 

ፕሮፌሰሩ አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ለመንግሥት ያደረጉትን ቀረቤታ በመጥላት አደጋ ሊያደርስባቸው የሚችል የኦነግ እንቅስቃሴ ፍንጭ ታይቷል በሚል ጥበቃው የተጠናከረላቸው ሲሆን በየሄዱበት እንደሚጠበቁም ለማወቅ ተችሏል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው እሁድ በትውልድ ሥፍራቸው በኦሎንኮሚ ከተማ የኦሮሚያ መንግሥት ልዩ ዝግጅት በማድረግ ልዩ አቀባበል በሚያደርግላቸው ወቅት ስምንት ወጣቶች መፈክር በመያዝ አስደንጋጭ ስልፍ አድርገዋል።

 

ያልተጠበቀውን ሰለማዊ ሰልፍ ያደረጉት እነዚህ ወጣቶች ከክልሉ ፕሬዝዳንት ከአቶ አባዱላ ገመዳና ከፕሮፌሰር ገቢሳ እጃታ ያለምንም ንግግር መፈከሩን ይዘው የቆሙ ሲሆን ወጣቶች በተደጋጋሚ የኦሎንኮሚ ከተማ ወደ ወረዳ ደረጃ ከፍ እንድትል ለጠየቁት ጥያቄ መልስ በማጣታቸው አጋጣሚውን ተጠቅመዋል ተብሏል።

 

ባለሥልጣናቱን ያስደነገጠው ይህ ድንገተኛ መፈክር በፀጥታ ሃይሎችና በሽማግሌዎች ሊዳኝ ያልቻለ ሲሆን የፀጥታ ኃይሎችን ሙከራ ሕዝቡ በጩኸት በመቃወሙ የክልሉ ፕሬዝዳንቱ ለወጣቶች ጥያቄ መልስ ለመስጠት ተገደዋል።

 

ጥያቄያችሁ ተመክሮበት መልስ ይሰጣችኋል በመባላቸው ወጣቶቹ ከሕዝቡ ጋር የተቀላቀሉ ሲሆን ፕሮፌሰር ገቢሣ በበኩላቸው የወጣቶቹን ድርጊት በማድነቅ “በሁከትና በረብሻ ጥያቄ ከማቅረብ ይህን በመሰለ ሰላማዊ መንገድ ጥያቄ ማቅረብ ዲሞክራሲያዊነት ነው በዚሁ ቀጥሉ ብለዋቸዋል።

 

ከዝግጅቱ በኋላ ወጣቶቹ ምን እንደደረሰባቸው ማወቅ ባይቻልም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጥቂት ሰዎች በኢትዮጵያ የተቃውሞ ሰልፍ በመወጣት ተቃውሟቸውን ማሰማት የጀመሩ ሲሆን በጥቅምት 15ቱ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመር ምክንያት አንድ ወጣት “በነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ምክንያት ኑሮን መቋቋም አልቻልኩም” በሚል ብቻውን ሰላማዊ ሰልፍ መወጣቱ የሚታወስ ነው።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ