ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የታሰሩበትን አንደኛ ዓመት የሚያስብ ዝግጅት ተጀምሯል
የፖለቲካ እስረኞች ወር
መታሰቢያው ለአንድ ወር የሚዘልቁ ዝግጅቶችን ያካትታል
የ37 ዓመቷ የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አለአግባብ ከመንገድ ታፍነው ተወስደው የታሰሩበትን አንደኛ አመት የሚያስብና እሳቸውንና ሌሎች በፖለቲካ እምነታቸው ምክንያት የታሰሩ ኢትዮጵያዊያንን ለማስፈታትና ጫና ለማሳደር የሚደረግ ለአንድ ወር የሚቆይ ዝግጅት እየተዘጋጀ መሆኑን የ “ነጻነት ለብርቱካንና ለሁሉም የህሊና እስረኞች” የተሰኘው ግብረሀይል እና ሌሎች የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ጊዜያዊ አስተባባሪ ኮሚቴ አስታውቋል።
ዝግጅቱ እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከዲሴምበር አጋማሽ 2009 እስከ ጃንዋሪ አጋማሽ 2010 የሚካሄድ መሆኑን የጠቀሰው ይሄው አስተባባሪ ኮሚቴ ዝግጅቱ አለም አቀፍ ከተሞችን የሚያሳትፍ መሆኑንና አምነስቲ አለምአቀፍን ጨምሮ ሌሎች አለም አቀፍ የሰብአዊ ተቋማትም እንደሚሳተፉ ገልጧል። እስካሁን ድረስ የዋሽንግተን ዲሲ፣ የቦስተን፣ የአትላንታ፣ የለንደንና የቶሮንቶ፣ ቫንኩቨር፣ የሳን ዲየጎና የፍራንክፈርት ከተሞች በዚህ ዝግጅት እንደሚሳተፉ የተረጋገጠ ሲሆን ሌሎች ከተሞችም ቀስ በቀስ ወደ እንቅስቃሴው እንደሚገቡ ያላቸውን እምነት የአስተባባሪ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ግርማይ ግዛው ገልጸዋል።
ዝግጅቱ የአለምአቀፍና ኢትዮጵያዊ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች እንዲሁም የሴቶችና የሙያ ማህበራት፣ ጋዜጠኞች፣ የጥበብ ባለሙያዎችና ሙዚቀኞች እንዲሁም ታዋቂ ሰዎች የሚሳተፉበት ሲሆን ሰልፍን፣ ስብሰባን፣ የስነጽሁፍና የሻማ ምሽትን፣ ሲምፖዚየምንና የብርቱካን ቤተሰቦችንና ሌሎች የህሊና እስረኞችን ለመርዳት የሚደረግ የገንዘብ ማሰባሰብን ያካትታል። በተለይ የዚህ ዝግጅት ማእከል በምትሆነው በዋሽንግተን ዲሲ ሰኞ ጃንዋሪ 11 ቀን 2009 በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ፊት ለፊት ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ የሚደረግ መሆኑንና የአሜሪካ መንግስትም ከሕወሀት/ኢህአዴግ ጋር አብሮ በመስራት የጥፋትና የታሪክ ተጠያቂ ከመሆን እንዲታቀብ ጥሪ የሚያቀርብ ሰልፍ እንደሚደረግ ታውቋል። በዚህ ዝግጅት የአንድነት የድጋፍ ቻፕተሮች በሙሉና ሌሎች መሰል የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች በአስተባባሪነትና በተሳታፊነት እንደሚገኙም ታውቋል።
ይሄንን ዝግጅት የሚያሰናዳው ኮሚቴ የስልክ ውይይት ላለፉት ሁለት ሳምንታት እንደተካሄደና ከየአገሩ የተወጣጡ ሌሎች ኮሚቴዎችም ስብሰባ በቀጣይነት እንደሚዘጋጅ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ግርማይ ግዛው ከአትላንታ ጨምረው ገልጸዋል።



