ብሪትሽ ካውንስል 50 ሠራተኛ ሊቀንስ ነው
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ኅዳር 22 ቀን 2002 ዓ.ም. December 1, 2009)፦ በኢትዮጵያ “ብሪትሽ ካውንስል” 50 ሠራተኞቹን ከሥራቸው ሊያሰናብት በዝግጅት ላይ መሆኑን ውስጥ አዋቂ ምንጮች ገለጹ።
የእንግሊዝ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በየሀገሩ ላቋቋማቸው የካውንስል ጽ/ቤቶች (ተቋማት) መድቦት የነበረውን በሚሊዮን የሚቆጠር በጀት ሀገሪቱን በገጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት ለማቀብ ተገዷል።
በመሆኑም ኢትዮጵያን ጨምሮ በየሀገሩ የሚገኙ የብሪትሽ ካውንስል ተቋም ሠራተኞች ከሥራ የመሰናበት ስጋት የተደቀነባቸው መሆኑን ውስጥ አዋቂዎች ይፋ አደረጉ። ስጋቱ ይኑር እንጂ እንግሊዝ ከሥራ ለምታሰናብታቸው የቀድሞ ሠራተኞችዋ ሞቅ ያለ የዋስትና ክፍያ ለመክፈል ቅድመ ዝግጅቷን ማጠናቀቋል ለማወቅ ተችሏል።
ብሪቲሽ ካውንስል በቅርቡ በአዲስ አበባ ለ50 ዓመታት የቆየበትን ሕንፃውን በደህንነት ስጋት በመልቀቅ ኤምባሲው ቅጥር ግቢ ውስጥ ወዳስገነባው ሕንጻ የተዘዋወረ ሲሆን፤ በቤተ-መጽሐፉ የነበሩትን መጻሕፍቶች ለወመዘከር ማስረከቡ ይታወቃል።



