የቡና አምራች ገበሬዎች መንግሥትን አማረሩ
Ethiopia Zare (ሐሙስ ኅዳር 24 ቀን 2002 ዓ.ም. December 3, 2009)፦ በደቡብ ክልል የወላይታ ቦዲቲ አካባቢ በቡና ማምራት የተሠማሩ ነጋዴዎች በዶ/ር እሌኒ የሚመራውን የመንግሥት ገበያ ቁጥጥር ድርጅት ሊያሰራን አልቻለም በማለት ምሬታቸውን አሰሙ።
አምራቾቹ ድርጅቱ እያደረገባቸው ያለው ነፃነትና ተአማኒነትን የሚያሳጣ ቁጥጥር በመንግሥት ላይ ከፍተኛ ቅሬታ እንዲያደርባቸውና ስራቸውንም በአግባቡ እንዳይወጡ ማድረጉን ለምንጮቻችን ገልጸዋል።
መንግሥት በቡና መሰብሰቢያ ወቅት ገበሬዎቹ ለመንግሥት እንዲያስረከቡ ከተተመነላቸው ኩንታል በታች ካስገቡ በኮንትሮባንድ እንደሸጡትና ለነጋዴዎች እንዳስረከቡ በመቁጠር ተአማኒነት ማጣታቸው እንዳማረራቸው ገልጸው ከመንግሥት የሚገኘው ገቢ አነስተኛ ቢሆንም በምንም ዓይነት ለነጋዴ መሸጥ እንደማይችሉ ተናግረዋል።
ከቡና የሚኖራቸው ተጠቃሚነት እያነሰ በመምጣቱ ያፈሉትን ችግኝ በሊዝ ለሚገዛቸው የሚሸጡ መሆናቸውን የገለጹት ገበሬዎቹ ሆኖም በሊዝ የገዛው ሰው ቡናውን የሚሸጠው በራሱ ስም ሳይሆን በባለ መሬቱ ስም ከመሆኑም በላይ ምርት አንድ ጊዜ ሊጨምር ሌላ ጊዜ ሊቀንስ ይችላል። ባለመሬቱም ሆነ ተከራይ ገበሬው በቂ ምርት ካላገኘ መንግሥት የመደበውን ከየትም ማምጣት አይችልም ብለዋል።ነጋዴዎቹ።
ነጻ ገበያ በተባለበት ሀገር ገበሬው በምርቱ ተጠቃሚ እንዳይሆን የሚደረገው ቁጥጥር ነጻነቱን ጥያቄ ውስጥ ይከታል፣ ነጋዴዎችን ቢቆጣጠሩ ዶላርን መውጣት መወረድ እያዩ ስለሚልኩ ነው እኛን መቆጣጠርና ትንፋሽ እስክናጣ ወጥሮ መያዝ ግን መብታችንን መግፈፍ ብቻ ሳይሆን ኑሯችንንም ማቃወስ ጭምር ነው ሲሉ የቡና ገበሬዎቹ ይፋ አድርገዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባ የቡና ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ሲሆን በጥቂት ወራት ውስጥ ከ30 ብር ይሸጥ የነበረው ኪሎ ቡና ወደ 50 ብር አሻቅቧል።



