ወ/ት ብርቱካንን ለማስፈታት 50 ሺህ ሰዎች በአስር ቀናት ፈረሙ
Ethiopia Zare (ዓርብ ታህሳስ 2 ቀን 2002 ዓ.ም. December 11, 2009)፦ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ከወህኒ ለማስፈታት የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የሴቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በአዲስ አበባ ብቻ 50 ሺህ ሰዎች በአስር ቀን ውስጥ ማስፈረሙን ገለጸ።
የሴቶች ጉዳይ ኃላፊዋ ወ/ሮ ላቀች ደገፉ እንደገለጹት የፓርቲያቸውን ሊቀመንበር ቀደም ሲል የተሰጣቸው ይቅርታ ጸንቶ ከወህኒ እንዲለቀቁ መንግሥትን በሚጠይቅ ሰነድ ላይ ነው ፊርማው የተሰበሰበው።
ፊርማ ማሰባሰቡ በፓርቲው የሴቶች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የበላይነት የሚከናወን ቢሆንም፤ በፓርቲው እውቅና አለው ያሉት ወ/ሮ ላቀች፤ ለሁለት ወር ያህል የፊርማ ማሰባሰቡ ተከናውኖ ካበቃ በኋላ ለተወካዮች ምክር ቤት፣ ለሀገር ውስጥ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማትና ድርጅቶች፣ እንዲሁም ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አምነስቲ ኢንተርናሽናል በውጭ ከሚኖሩ የአንድነት ደጋፊዎች ጋር በመተባበር ተመሳሳይ የፊርማ ማሰባሰብ ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ የአምነስቲ ፊርማ ማሰባሰብ ሲጠናቀቅ ለአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለሚስ ሂላሪ ክሊንተና ለትላልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚላክ መሆኑ ታውቋል።
ወ/ሪት ብርቱካን እስር ቤት ከገቡ ታህሳስ 20 ቀን 2002 ዓ.ም. (ከ18 ቀን በኋላ) አንደኛ ዓመታቸውን ይይዛሉ። አምነስቲ ባዘጋጀው የፊርማ ማሰባሰብ ሂደት ላይ ለመሳተፍ እዚህ ይጫኑ!



