እግረኞችንና ለማኞችን የሚቀጣ ህግ ወጣ
Ethiopia Zare (ሰኞ ታህሳስ 12 ቀን 2002 ዓ.ም. December 21, 2009)፦ እግረኞች ከሰኞ ጀምሮ በዜብራ መንገድ የማይሄዱ ከሆነ በትራፊክ ፖሊሶች ቅጣት እንደሚወሰንባቸው የትራፊክ ፖሊስ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሳጅን አሰፋ መዝገቡ ገለጹ።
ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዳር 24 ቀን 2002 በፓርላማ የጸደቀው ሕግ ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነው ዜብራ የማይጠቀሙ መንገደኞችን ብቻ ሳይሆን በመንገድ ዳር ለሚለምኑና ገንዘብ የሚሰጡትንም ቅጣቱ ይመለከታል ተብሏል።
ከ20 እስከ 60 ብር ድረስ የሚያስቀጣው ይህ ሕግ በነጋሪት ጋዜጣ ሲወጣ በዝርዝር የሚገለጽ ሲሆን ትራፊኮች ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ሕጉን ተፈጻሚ እንደሚያደርጉ ተገልጿል።
በትራፊክ ፖሊስ የሚያስቀጡ አዲሶቹ ሕጎች ስልክ እያነጋገሩ ማሽከርከር፣ ቪዲዮ እየተመለከቱ መንዳት፣ የደህንነት ቀበቶ ሳያስሩ ማሸከርከር፣… በትራፊክ ደንብ መተላለፍ ወንጀል ያስጠይቃል።
በተጨማሪም በጎዳና ላይ ንግድ እና ልመናም ከሚያስቀጡ ስራዎች የሚመደቡ መሆኑ ታውቋል።
በአዲስ አበባ ያሉ ዘመናዊ መንገዶች ነባሮቹም ሆኑ አዲሶቹ በነጭ የተሠመረው የዜብራ መስመር ያለው ከ60 በመቶ ብቻ እንደሆነ የሚታወቅ ሲሆን መሥመር በሌለባቸው የከተማ ዋና ዋና መንገዶች ላይ ህጉ እንዴት ተፈጻሚ እንደሚሆን የተገለጸ ማብራሪያ የለም።



