በቫንኩቨር ብርቱካን ሚደቅሳ የታሰረችበት አንደኛ አመት ተከበረ
በተክለሚካኤል አበበ
ሰፊ ውይይትም ተደረገ
በቫንኩቨር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን በታህሳስ 20 2001 ዓ.ም. በወያኔ ወታደሮች ያለአግባብ ተይዛ ቃሊቲ እስር ቤት የተወረወረችውን የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ መሪ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የታሰረችበትን አንደኛ ዓመት አክብረው ዋሉ።
እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር፡ ቅዳሜ ታህሳስ 27 ከቀኑ አራት ሰዓት እስከ 7 ተኩል ሰዓት በተካሄደው በዚሁ ስብሰባ ላይ ብዛት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን የተገኙ ሲሆን ነዋሪነታቸው በሲያትል የሆነውና የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ፕሮፌሽናል የካርታ ስራ ባለሙያ አቶ ዘውገ ፈንታ ንግግር አቅርበዋል። አቶ ዘውገ ፈንታ ብርቱካን አንደኛ እውቅናን እያገኘች በመምጣቷ፤ ሁለተኛ አቶ መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ ህዝብ ንቀት ስላላቸውና ህዝቡን ለማስፈራራት ሲሉ እንደታሰረች ተናግረዋል።
የብርቱካን እስራትም የኢትዮጵያን ህዝብ እስራት እንደሚያሳይ ጨምረው ተናግረዋል። አቶ ዘውገ አስከትለውም ሰው ለማሸነፍ የግድ ይታሰር ማለት ባይቻልምና ወያኔ ብርቱካንን ያሰራት ሞራሏን ለመስበርና ለመርታት ቢሆንም ብርቱካን ግን ከእያንዳንዱ በእስር ቤት ከምታሳልፈው ሴኮንድ፤ በኢትዮጵያዊያን ዘንድ፡ ያስር ዓመት ክብር እንደምታገኝ ተናግረዋል።
አቶ ዘውገ በተጨማሪም፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አፋኝ ስርአት ጸረ-ኢትዮጵያ ከመሆኑ የተነሳ የኢትዮጵያን ድንበር ለሌሎች አገሮች አሳልፎ እየሰጠ መሆኑን ተናግረዋል። የመጀመሪያውን ባለቀለም የኢትዮጵያንና የአዲስ አበባን ካርታ የሰሩትና በልጅነታቸው ላገራቸው ባበረከቱት ከካርታ ጋር የተገናኘ ስራ በጃንሆይ ዘንድ ቀርበው የተሸለሙት፤ በኋላም የትምህርት እድል አግኝተው ወደአሜሪካን የመጡት አቶ ዘውገ ፈንታ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ፤ በወያኔ ለሱዳን አሳልፎ የተሰጠውን በሰሜን ምእራብ ከተሰነይ እስከ በጎንደር ሁመራ አልፎ እስከ ኦሜድላ የሚደርስ መሬት ተዘዋውረው እንዳጠኑና ካርታውንም እንደሰሩ፤ የወያኔው መሪ አቶ መለስ ባንድ በኩል ኢትዮጵያ ምንም መሬት ለሱዳን አልሰጠችም ብለው በሌላ ቀን ደግሞ ከሱዳን የወሰድነውን መሬት መልሰን ሰጥተናል ማለታቸው ርስ በርሱ የሚቃረን መሆኑን ጠቁመዋል።
አቶ ዘውገ በተጨማሪም ኢትዮጵያ አሁን የምትመራበት ቋንቋን መሰረት ያደረገ ፌደራሊዝም ለኢትዮጵያ የማይበጅና ከፋፋይ መሆኑን ጠቁመው እሳቸው ለኢትዮጵያ ይበጃል ስለሚሉት የመሬት አቀማመጥንና ታሪክን መሰረት ያደረገ የአስደዳደር አወቃቀር ተናገርዋል።
ከአቶ ዘውገ ንግግር በተጨማሪም በብርቱካንና በድንበር ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይት ተደርጐ የእለቱን ዋና ጉዳይ የብርቱካንን መታሰር መሰረት ያደረገ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዝግጅተም ተደርጓል።
በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በሰፊው በመንቀሳቀስ የሚታወቁት አቶ ከበደ ሀይለማሪያም የብርቱካንና የልጇ ምስል ያለባቸውን የቡናና ሻይ ኩባያዎች አቅርበው ሁሉም ተቸብችበው ገቢው ለብርቱካን ሚደቅሳ ቤተሰቦች እንዲላክ ሰጥተዋል። በእለቱ አንዳንድ ኢትዮጵያዊያን የኢትዮጵያን ህዝብ መንገፍገፍ የሚጠቁሙ አልባሳትን ለብሰው ተስተውለዋል።
ከኢትዮጵያ ተሰደው ነዋሪነታቸው በካናዳ የሆነው ወ/ት አለምጸሀይ ዳምጤ “በቃ” የሚውን ካኒቴራ ለብሰው የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ/ኢህአዴግ አገዛዝ ምን ያህል እንደተንገፈገፈ ተናግረዋል።
ታህሳስ 27፡ 2009 ዓ.ም.



