በአዲስ አበባ ከአስር ሺህ በላይ የቤት ባለቤትነት ሰነዶች መክነዋል
Ethiopia Zare (ሰኞ ታህሳስ 26 ቀን 2002 ዓ.ም. January 4, 2010)፦ በአዲስ አበባ የተለያዩ ክፍለ ከተሞች ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ የቤት ካርታዎችና ሰነዶች በመዝገብ ቤት ውስጥ ሊገኙ አለመቻላቸውንና መምከናቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።
ምንጮቹ እንደገለጹት የረጅም ጊዜ የግለሰብና የመንግሥት ይዞታ ሆነው የተመዘገቡ ቤቶች ካርታዎቻቸው በማዘጋጃ ቤቱ ማኅደር ሊገኙ አልቻሉም።
በቅርቡ ከመንግሥት ባንክ በዕዳ ተይዞ የነበረ አንድ ቤት ባንኩ ባወጣው ጨረታ መሠረት ለአሸናፊው ግለሰብ ቤቱን ለማስረከብ ማስረጃዎች በሚታዩበት ወቅት ነው የካርታው መምከን የታወቀው። ተያይዞ በተደረገ ፍተሻም የበርካታ ድርጅቶችና መኖሪያ ቤቶች ካርታዎች መምከናቸው ታውቋል።
የካርታ መምከን የባለ ይዞታ ባለቤትነትን፣ የይዞታው መጠንን፣ የይዞታው ክልልን፣ በሙሉ መጥፋትን የሚያመለክት በድጋሚ እንደአዲስ ለመሥራት ካልሆነ የማይቻልና በዚህም ከፍተኛ የማጭበርበርም ሆነ ስህተት የበዛበት ሁኔታ እንደሚያጋጥም የማዘጋጃ ቤት ምንጮች ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
በተያያዘ ዜና ከ1995 ዓ.ም. ጀምሮ የተሠረቁ ፋይሎች በየክፍለ ከተሞች መገኘታቸው ታውቋል። የክፍለ ከተማ የኢህአዲግ አባላትና ሹሞች አቶ አርካበ ዕቁባይ የማዘጋጃ ቤቱ ከንቲባ በነበሩበት ወቅት ተፈጥሮ በነበረ ሹም ሽር ጥቅማቸውን ሲያስከብሩ የነበሩ ባለሥልጣናትና ከዚያም በኋላ በጊዚያዊ አስተዳደሩ በአቶ ብርሃነ ዴሬሣ ወቅት የነበሩ ባለሥልጣናት የክፍል ከተሞችን የመሬት ይዞታ ፋይል ከተደበቁበት እየተገኘ ሲሆን፤ የኮልፌ ክፍለ ከተማ ፋይል ቂርቆስ ክፍለ ከተማ፣ የጉለሌ የካ፣ የየካ አቃቂ ክፍለ ከተማ እየተገኘ መሆኑና ለማወቅ ችለናል።
የማዘጋጃው ምንጮች እንደጠቆሙት ፋይላቸው የጠፋባቸው በርካታ አመልካቾች ፋይላቸውን ፍለጋ የመጡ ሲሆን፤ አንዳንዶቹ ሲሳካላቸው የአብዛኞቹ የመሬት ባለቤቶች ፋይል በየክፍለ ከተማው እየተፈለገ ይገኛል ብለዋል።



