በኢትዮጵያ ለውትድርና ጥሪ ቀረበ
Ethiopia Zare (ዓርብ ታህሳስ 30 ቀን 2002 ዓ.ም. January 8, 2010)፦ በኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ድርጅት በወትድርና ሙያ የሚሠማሩ መስፈርቶችን በማስቀመጥ የውትድርና ምልመላ ጥሪ አቀረበ።
ገዥው ፓርቲ በሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኀን በተሠራጨው በዚሁ ጥሪ ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነውና 12ኛ ክፍልን ያጠናቀቀ ሙሉ ጤነኛ ወጣት እንደሚፈለግ ያመለክታል።
በያዝነው ሣምንት መጀመሪያ የኤርትራ ባለሥልጣናት በዛላምበሳ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ተኩስ እንደከፈተባቸው ከገለጹ በኋላ በሁለቱ መንግሥታት የመገናኛ ብዙኀን (በቴሌቭዥን) ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች በማሳየት ላይ ይገኛሉ።
የኤርትራ መንግሥት ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ በዛላምበሳ ጥቃት ፈጽማብኛለች ቢልም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ኤርትራን የሚፋለሙ ተዋጊዎች ጥቃት መሰንዘራቸውንና ሰብዓዊ ኪሳራ ማድረሳቸውን ነው ያሳወቀው።
በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት በኤርትራ መንግሥት ላይ በጣለው ማዕቀብ ምክንያት የኤርትራ መንግሥት አዲስ የትኩረት ስልት እንደመረጠ የሚገልጹት ተንታኞች ኢትዮጵያን በመተንኮስ ወደ ጦርነት ለማስገባት ሳያቅድ አይቀርም የሚል ግምታቸውን አስፍረዋል። ሌሎች ተንታኞች ደግሞ በኤርትራ ላይ የተጣለውን ማዕቀብ በመጠቀም ከዓለማቀፉ ማኅበረሰብ ትርፍ ለማግኘት የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነት ሊቀሰቅስ ይችላል ሲሉ አስተያየት ሲሰጡ ተሰምተዋል።



