Ethiopia Zare (ቅዳሜ ጥር 8 ቀን 2002 ዓ.ም. January 16, 2010)፦ምርጫ 2002ን አስታኮ በየክልሉ ያሉ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት እስርና እንግልት እየተባባሰ መምጣቱን የየፓርቲዎቹ አመራሮች እየገለጹ ነው።

 

ኦፌዲን በወለጋና በኢሉአባቡር አባላቶቼ እየታሰሩ ነው መሆኑን ሲገልጽ፤ ኦህኮ ደግሞ በአምቦ በአባላቶቹ ላይ የጅምላ እስር በሌሎችም ክልሎች ደጋፊዎቹና አባላቶቹ መታሰራቸውን ገልጿል። አንድነት በበኩሉ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ክልሎች በአባላቱ ላይ ውክቢያ እየተፈጸመባቸው መሆኑን ገልጿል።

 

በቅርቡ በመቀሌ የተሳካ ህዝባዊ ስብሰባ ማካሄዱን የገለጸውና በኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል የሚመራው መኢአድ ከመቀሌ መልስ በተያዩ ከተሞች ቅስቀሳ ሲያካሂድ የልዑካን ቡድኑ በደብረብርሃን ከተማ በሚገኙ የአገዛዙ ካድሬዎች ከፍተኛ ወከባና እንግልት ደርሶባቸው እንደነበር ድርጅቱ ይፋ አድርጓል።

 

በ1997 ዓ.ም. ምርጫ የተቃዋሚዎችን እንቅስቃሴ ለማፈን በገዥው ፓርቲ ኃይሎች ሲደረግ የነበረው አይነት እንቅስቃሴ ከወዲሁ መጀመሩን የሚገልጹት አንድ የአንድነት አባል፤ “ምንም ስጋት የለብኝም መቶ በመቶ የማሸነፍ ዕድል አለኝ የሚለው ኢህአዲግ ፍርሃቱ እያገረሸበት ገላመጥከኝ በሚል ሰበብ እንኳ ሳይቀር የተቀናቃኝ ፓርቲ አባላትን እያሰረ ነው” ብለዋል።

 

መድረክ 23 እጩዎችን ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ያቀረበ ሲሆን፤ ለ2002ቱ የፓርላማ ምርጫ ከ500 በላይ እጩዎችን ለክልል ምክር ቤቶች ደግሞ 1500 እጩዎችን እንደሚያቀርብ ለማወቅ ተችሏል።

 

መድረክን የተቀላቀሉት ስምንት ድርጅቶች በምርጫው ላይ ያላቸውን ስጋት ይፋ በማድረግ እስካለመወዳደር እንደሚደርሱ እየገለጹ ሲሆን፤ በግንቦት ወር ለሚካሄደው ምርጫ አራት ወራት ብቻ መቅረቱ ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ