ጥቁር ሳጥኑ ተገኘ

የሠራተኞች ስም ዝርዝር ይዘናል

Ethiopia Zare (ሐሙስ ጥር 20 ቀን 2002 ዓ.ም. January 28, 2010)፦ በኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር ET-409 በተከሰተው አሰቃቂ አደጋ ከሞቱት 90 ሰዎች መካከል የ36ቱ አስከሬን የተገኘ ሲሆን፤ በበረራ ሥራ ላይ የተሰማሩት የአየር መንገዱ ሠራተኞች ማንነት መታወቁን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።

 

ከቤይሩት ወደ አዲስ አበባ ይበር በነበረውና የአውሮፕላኑን ሠራተኞች ጨምሮ 90 ተሳፋሪዎችን ይዞ ይጓዝ የነበረው ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ላይ በደረሰው አሰቃቂ አደጋ መነሻ ምክንያት እስካሁን ያልተረጋገጠ ቢሆንም፤ የአደጋ ጊዜ የመረጃ ምስጢር መሰብሰቢያው ሳጥን ከመሬት በታች 1300 ሜትር ጥልቀት ከቤይሩት 8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ተገኝቷል። የአደጋው መነሻ በአካባቢው የነበረው ከመብረቅ ጋር የተቀላቀለ ከባድ ዝናብ ከመሆኑ ውጭ ምንም አይነት ፍንጭ እስካሁን አልተገኘም።

 

በበረራው ሥራ ላይ ከነበሩት የበረራ ክፍል ባልደረቦች ውስጥ ዋና አብራሪው ሐብታሙ በንቲ እና ረዳት አብራሪው አሉላ ታምራትን ጨምሮ ኅሊና አዲስ፣ ሰብለወንጌል ስዩም፣ ነፃነት ይፍሩ፣ ገሊላ ጌዲዮን፣ ሰብለ ገ/ጻዲቅ እንደሚገኙበትና አንድ ስሙ ያልታወቀ የበረራ ክፍል ባልደረባም እንደነበር ለመረዳትችለናል።

 

በዚህ በያዝነው ሣምንት ሰኞ ንጋት ላይ በተከሰተው በዚሁ አደጋ 90 ሰዎችን ከያዘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን እስካሁን በሕይወት የተረፈ ሰው ያልተገኘ ሲሆን፤ ብዛት ያላቸው የሊባኖስ እና የኢትዮጵያ ዜግነት ያላቸው ሰዎች የአደጋው ተጠቂዎች መሆናቸው ይታወቃል።

 

አደጋው በአካባቢው በነበረው ከባድ አየር ንብረት ምክንያት ተከሰተ መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች ቢታዩም፤ የሊባኖስ የበረራ መቆጣጠሪያ ሠራተኞች ከአብራሪው ጋር የነበራቸውን ግንኙነት እንደምክንያት ሲጠቅሱ ተደምጠዋል። የጥቁር ሳጥኑ የምርመራ ውጤት የአደጋውን ዋና ምክንያት ይገልጻል ተብሎ ይጠበቃል።

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለዘመናት በአፍሪካ አስተማማኝ የበረራ ተቋም መሆኑ ሲነገርለት መቆየቱ ይታወቃል።

 

በዚህ አጋጣሚ በዘግናኙ አደጋ ሕይወታቸውን ላጡና በኀዘን ላይ ለሚገኙ ወዳጅ ዘመዶች ሁሉ የተሰማንን ጥልቅ ኀዘን በመግለጽ፤ አምላክ ብርታቱን ይሰጣችሁ ዘንድ የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ትመኛለች!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!