“የአንድነት መንፈሥ ያላቸው ኢትዮጵያና ኤርትራ መዋሃድ አለባቸው” ኮ/ል አምሳሉ ገብረዝጊ ገብሩ
Ethiopia Zare (ዓርብ መጋቢት 17 ቀን 2002 ዓ.ም. March 26, 2010)፦ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ዳግማዊ የህዝብ ውህደትና አንድነት ለማምጣት መንግሥትን መጠበቅ አያስፈልግም ተባለ። ይህን ያሉት በጥር ወር 11ኛ ቀን 2002 ዓ.ም. “የኤርትራ መዘዝ” የተሰኘ መጽሐፋቸውን ለአንባቢያን ያደረሱት፣ ኮሎኔል አምሳሉ ገብረዝጊ ገብሩ የተባሉት የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አዛዥ ናቸው።
በመጽሐፋቸው ላይ “የኢትዮጵያና የኤርትራ ህዝቦች ወንድማማችነትና ታሪካዊ ትስስር በጥቂት ሰዎች ፍላጎት የሚወሰን አይደለም” ያሉት ኮሎኔሉ፤ በአሁኑ ወቅት አሥመራና አዲስ አበባ ባሉት መንግሥታት መካከል ለድርድር አመቺ የሆነ ነገር እንደሌለ ጠቁመው፤ “በተለይ በውጭ ሀገር የሚኖሩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ምሁራን ኃላፊነት ተሰምቷቸው የተለያዩትን ህዝቦች ለማገናኘት መሥራት አለባቸው” ብለዋል። ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ልባዊ እምነት ይዞ መንቀሳቀስና ጥላቻን ማራቅ እንደሚገባም ኮሎኔል አምሳሉ አስገንዝበዋል።
እኔ ከሕይወትና ከሥራ ልምዴ፣ በኤርትራ ምድር ካደረኩት ቆይታ የተረዳሁት ሐቅ “ሁለቱ ህዝቦች የአንድነት መንፈሥ እንዳላቸው ነው” በማለት አባባላቸውን በማስረጃ የሚያስደግፉት ኮሎኔሉ፤ “ኢትዮጵያና ኤርትራ ሊነጣጠሉ የማይችሉባቸው ብዙ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የባህል፣ የሥነ-ምግባር፣ … ዝምድና አሏቸው። እነዚህም ያስተሳስሯቸዋል። ያዋህዷቸዋልም። ...” ብለዋል።
የኤርትራ ህዝብ ከባንዲራና ከባዶ የነፃነት ልፈፋ ውጪ ምንም አማራጭ አለማግኘቱን፣ የሁለቱም (የኢትዮጵያና የኤርትራ) ህዝቦች በግልጽም ሆነ በድብቅ የአንድነት ጥያቄ ሲያነሱ የሚሰጣቸው መልስ መጥፎ ነው፣ እንደ ዜጋም ሃሳባቸውን የመግለጽ ነፃነት የላቸውም፣ … የሚሉት ኮሎኔል አምሳሉ ገብረዝጊ፤ ችግሩ ለህዝብና ለምሁራን ካልተተወ በቀር “የኤርትራ ጉዳይ ገና ብዙ መዘዝ ይኖረዋል፤ በባድመም ይሁን በሌሎች ምክንያቶች አሁንም የጦርነት ዳመና አንዣቧል”፤ ኢትዮጵያውያን የሆንን የሁለቱ ሀገር ሰዎች “በፈንጂ አጥር ስለተነጣጠልን ተገናኝተንና ተቀራርበን መነጋገር አልቻልንም” የሚለውን ሃሳብ በአጽንዖት ገልጸውታል።
ኮሎኔሉ፤ “የኤርትራ መዘዝ” በተሰኘው መጽሐፋቸው፤ በሊቀመንበር መንግሥቱ ኃ/ማርያም ጊዜ የነበረውን የኢትዮጵያን ጦር እንቅስቃሴና የግዳጅ አፈፃፀም፣ የአዛዥ ታዛዥ ግንኙነት ብሎም በኤርትራ መሬት የጦሩን ሽንፈት ምክንያት ከራሳቸው ዕይታ አኳያ ነቅሰው አውጥተዋል።
ዘግናኝ የወትድርና ዘመኔ አጋጣሚ ነበር ያሉትንም ሲያወሱ፤ “በግንቦት ወር 1980 ዓ.ም. በአፋ-ቤት ውጊያ ሻዕቢያ የማርካቸውን ከ100 የሚበልጡ የኢትዮጵያን ወታደሮች በመሬት ላይ አስተኝቶ በታንክ የሄደባቸውን ሁኔታ ነው” ብለዋል። ይህ የሻዕቢያን አረመኔነት የሚያንፀባርቅ ብቻ ሳይሆን፤ ከውጊያ ሕግ ውጪ የሆነ አሰቃቂ ተግባር መሆኑን ያመለከቱት ኮሎኔሉ፤ በሊቀመንበር መንግሥቱ ዘመን በተካሄደው ሥርዓት ተጎጂ የሆኑት የዛሬዎቹ ኤርትራዊያንና ኢትዮጵያውያን በሙሉ ናቸው። ውድመቱም በአንድ ወገን ብቻ የሚገለጽ አይደለም ብለዋል።
“የኤርትራ መዘዝ” የተሰኘው መጽሐፍ በርካታ ድብቅ ጉዳዮችን ይፋ ያደረገ ቢመስልም፤ ሌሎች የተሸፋፈኑ የኢትዮጵያና የኤርትራ ችግሮች መኖራቸውንም ጠቁሞ አልፏል። የመጽሐፉ ደራሲ ኮሎኔል አምሳሉ ገብረዝጊ፤ የሐረር ጦር አካዳሚ ምሩቅ እንደመሆናቸው ወደዚህ ጦር አካዳሚ ተመራቂ መኮንኖች ልዩና ታላቅ ወታደራዊ ሰውነት፣ የሀገርና ወገን አፍቃሪነት ምስክርነታቸውን በአብዛኛው ይገልጻሉ።
እኚህ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ባልደረባ፤ በሁለተኛው አብዮታዊ ጦር፣ በናደውና በመንጥር ዕዝ፣ በ19ኛ እና በ22ኛ ተራራ ክ/ጦር፣ በ23ኛ እግረኛ ክ/ጦር በም/አዛዥነት፣ በዘመቻ መኮንንነት፣ በትምህርት መምሪያ ኃላፊነት አገልግለዋል። በደርግ ውድቀት ዋዜማም በተዋጊነት ችሎታቸውና ጠላትን በማሸበሩ እጅግ ተደናቂና የወገን ኩራት የነበረው የ15ኛ እግረኛ ክ/ጦር አዛዥ ነበሩ።
ኮሎኔል አምሳሉ ገብረዝጊ የመጽሐፋቸውን መታሰቢያነት ለኢትዮጵያ አንድነትና ልዑላዊነት ለማስከበር ሲባል ለተሰዉ ውድ የኢትዮጵያ ልጆች በሙሉ አድርገዋል።



