የአንድነት ምክር ቤት አባል በመከላከያ መኪና ተገጩ
Ethiopia Zare (ረቡዕ መጋቢት 29 ቀን 2002 ዓ.ም. April 7, 2010)፦ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ዳዊት አስራደ፤ በመከላከያ ሠራዊት መኪና ተገጭተው በእግራቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ታወቀ።
ከአንድ ሣምንት በፊት በመከላከያ ሠራዊት ተሽከርካሪ አዲስ አበባ ከተማ እንጦጦ አካባቢ ከተገጩ በኋላ ወንጀሉን የፈጸሙት አካላት ማንነት ካለመታወቃቸውም ሌላ ምን አይነት እርምጃ እንደተወሰደባቸው የታወቀ ነገር እንደሌለ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።
አቶ ዳዊት አስራደ አደጋው ከደረሰባቸው ጀምሮ በዮርዳኖስ የግል ሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኙ ፓርቲያቸው አስታውቋል።
በአቶ ዳዊት ላይ ለደረሰው የመኪና አደጋ “የገዢው ፓርቲ እጅ አለበት” የሚሉ ወገኖች እስካሁን ምንም አይነት ፍንጭ አለመገኘቱን ገልጸዋል። የመኪና አደጋው የደረሰባቸው የአንድነት ም/ቤት አባል በእግራቸው ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል።



