በቫንኩቨር ከካናዳው የፓርላማ ተመራጭ ጋር ህዝባዊ ስብሰባ ይካሄዳል
ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ የካናዳ መግቢያ (ቪዛ) እንዳይሰጣቸው ከፍተኛ ዘመቻ ተጀምሯል
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሚያዝያ 2 ቀን 2002 ዓ.ም. April 10, 2010)፦ በካናዳ ብዙ ኢትዮጵያዊያን የሚኖሩባት የኒው ዌስት ሚኒስትርና በርናቢ አካባቢ የተወካዮች ምክር ቤት አባል አቶ ፒተር ጁሊያን ወ/ት ብርቱካንን ለማስፈታት በሚደረገው ጥረት ዙሪያና ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ከኢትዮጵያውያኖችና ካናዳውያን ጋር ለመምከር ስብሰባ ጠሩ።
በዚሁ ዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 10 ቀን 2002 ከቀኑ አስር ሰዓት (4 P.M.) ጀምሮ በሚካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ለካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወ/ት ብርቱካን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንድትፈታ መሠራት ስላለባቸው ሁኔታና በቅርቡ ለመሣሪያ መግዣ ዋለ ስለተባለው የእርዳታ ገንዘብ እንዲሁም ስለብርቱካን ሚደቅሳ የጤንነት ሁኔታ ውይይት እንደሚደረግ ከውይይቱ አዘጋጆች ለመረዳት ችለናል። የወ/ት ብርቱካን እስር ፖለቲካዊ ይዘት ያለው እንደሆነና መንግሥታቸው ትኩረት ሰጥቶ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ጫና እንዲፈጥር አቶ ፒተር በተደጋጋሚ መጎትጎታቸው ይታወቃል።
የፓርላማ አባል የሆኑት አቶ ፒተር ጁሊያንና በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ጠቅላይ ግዛት የNDP ፓርቲ ወኪል አቶ ራጅ ቹሀን በስብሰባው ላይ ተገኝተው ንግግር እንደሚያደርጉና ከህዝቡ ጋር የጥያቄና መልስ ጊዜ እንደሚኖራቸው ለመረዳት ተችሏል።
የፓርላማው ተመራጭ የወ/ት ብርቱካን እስር ዓለም አቀፍ ሕግጋት ከሚያዘው ውጪ ያለ ጠያቂ መታሰሯና ሕክምና መከልከሏ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት ራሱ ያወጣውን ሕግ የማያከብርና የተባበሩት መንግሥታት የእስረኛ አያያዝ ደንብ የጣሰ ነው በማለት በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጸዋል።
በተያያዘ ዜናም በመጪው ሰኔ ወር ላይ ወደ ካናዳ ለG8 ስብሰባ ይመጣሉ ተብለው የሚጠበቁት ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ እና ተከታዮቻቸው፤ ቀደም ሲል መንግሥትን በኃይል ለመጣል ሲዋጉ የነበሩ በመሆናቸውና ሥልጣን ከያዙም በኋላ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት በመጣሳቸው፣ እንዲሁም በዘር ማጥፋት ወንጀል የሚያስጠረጥራቸው ምክንያታዊ ሁኔታ ስላለ ወደ ካናዳ መግቢያ ፈቃድ እንዳይሰጣቸው ለማስከልከል ጥረት መጀመሩን ከስፍራው የደረሰን ዜና ያስረዳል።
ካናዳ በሽምቅ ውጊያ የተሳተፉ፣ በሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አያያዝ መጥፎ ስም ያላቸውን የማናቸውንም ሀገር ባለሥልጣናትም ሆኑ ግለሰቦችን ወደ ሀገሯ እንዳይገቡ የሚከለክል ሕግ ያላት ሀገር እንደመሆኗ፤ ጠ/ሚ መለስን ጨምሮ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስየም መስፍን እና የልዑካን ቡድናቸው ወደ ካናዳ እንዳይገቡ ለማድረግ በቫንኩቨር - ካናዳ ከፍተኛ እንቅስቃሴ መጀመሩንና የዚሁ ጥያቄ ማመልከቻም ለአቶ ፒተር ጁሊያን እንደሚቀርብ ለመረዳት ችለናል።
የካናዳ መንግሥት ቀድሞ መንግሥትን ለመጣል የሽምቅ ውጊያ ያደርጉ የነበሩ አማጽያን ላይ ያለው ፖሊሲ ጥብቅ ከመሆኑ የተነሳ በ2008 እ.ኤ.አ. የኤርትራውን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኦስማን ሳላህ መሀመድን የመግቢያ ፈቃድ (ቪዛ) የከለከለ ሲሆን፤ ይሄ ፖሊሲ በኢህአዲግ ባለሥልጣናትም ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን ተግተው እንደሚሠሩ የኮሚቴው አባላት ከማስታወቃቸውም በላይ በመላ ካናዳ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና የሰበአዊ መብት ተቋማት ተግተው እንዲሠሩበት አሳስበዋል።



