የኅሊና እስረኞች በገንዘብ ሊተመን የማይችል መስዋዕትነት ከፋዮች መሆናቸው ተገለጠ
ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳና ሌሎችም ኢትዮጵያዊያን የኅሊና እስረኞች የከፈሉትና በመክፈል ላይ የሚገኙት መስዋዕትነት በገንዘብ ሊተመንና ከቶም ሊካካስ የማይችል መሆኑ ተገለጠ። ይህ የተገለጠው፣ እ.ኤ.አ. ፌብሯሪ 6 ቀን 2010 በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት “ድጋፍና አክብሮት ለኅሊና እስረኞች” በሚል መርኅ በሂዩስተን ከተማ የተከናወነው በኢትዮጵያ የሚገኙ የኅሊና እስረኞች ማሰቢያና ድጋፍ ማሳያ ሥነሥርዓትን ያቀጋጀው ኮሚቴ በሰጠው ማብራሪያ ላይ ነው።
በግል ተነሳሽነት ዝግጅቱን ያከናወነው ኮሚቴ ሰሞኑን ባቀረበው የክንውን ዘገባ ላይ እንደተገለጠው፤ ለኅሊና እስረኛዋ ለወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ድጋፍ የተሰበሰበው ገንዘብ ለእስረኛዋ ቤተሰበ መድረሱ ማረጋገጫ ባቀረበበት ሥነሥርዓት ላይ መሆኑ ታውቋል። በዌስተርን ዩኒየን ዓለም አቀፍ የገንዘብ ማስተላለፊያ በኩል በብርቱካን ሚደቅሳ እናት ስም የተላከው $ 3000.00 (ሦስት ሺህ) የአሜሪካ ዶላር መድረሱን ያረጋገጠው የኮሚቴው ዘገባ፤ የታሳሪዋ ቤተሰቦች ድጋፉን ላደረጉት የሂዩስተን ከተማ ነዋሪ ኢትዮጵያውያን ልባዊ ምስጋና ማቅረባቸውንም አመልክቷል።
በኢትዮጵያ ነፃ ፕሬስ ጋዜጠኞች ማኅበር (ኢነጋማ) ፕሬዝዳንት ጋዜጠኛ ክፍሌ ሙላት የመድረክ አስተናባሪነት በተከናወነው የሂዩስተኑ ዝግጅት ላይ፤ አቶ ኦባንግ ሜቶ እንዲሁም የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ተወካይ ንግግር ማድረጋቸውና ኢትዮጵያውያን ለሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻቸው መከበር የጋራ ትግል ማድረግ እንደሚኖርባቸው ማስገንዘባቸው ይታወሳል። በድምፅና በምስል የተቀነባበሩ ዝግጅቶች በቀረቡበት፣ እንዲሁም የተለያዩ ግጥሞች በተነበቡበት መድረክ ላይ እውቁ አቀንቃኝ ሻምበል በላይነህ በተለያዩ ጣዕመ ዜማዎች ታዳሚዎቹን ማዝናናቱና ድምቀት መስጠቱ አይዘነጋም።
ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳና ሌሎችም ኢትዮጵያዊያን የኅሊና እስረኞች የከፈሉትና በመክፈል ላይ የሚገኙት መስዋዕትነት “በገንዘብ ሊተመንና ከቶም ሊካካስ የማይችል ነው” ያሉት የኮሚቴው አባሎች፣ የተጠቀሰው ገንዘብ የአጋርነት ማሳያ እንጂ ትልቅም፣ የመጨረሻም እንዳልሆነ መናገራቸው ታውቋል።
ከዚህም በተጨማሪ የሂዩስተን ከተማ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ጨዋነትን በተላበሰ ሥነምግባርና በወገን አፍቃሪነት ስሜት ያሳዩት መረባርብ ከልብ ያኮራቸው መሆኑን የአስተባባሪ ኮሚቴው አባሎች ገልጠዋል። አክለውም ለወደፊቱም የበለጠ በመጠናከር አስፈላጊ ሆኖ በሚገኘው ጊዜና ቦታ ሁሉ በአንድነት መቆም የዜግነት ግዴታ መሆኑን አሳስበው፣ ብርቱካን ሚደቅሳንና ሌሎችም የኅሊና እስረኞች እስከሚፈቱ ድረስ ድጋፉና ግፊቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የጠ/ሚ መለስ ዜናዊ አገዛዝ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳንና ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ የኅሊና እስረኞችን እንዲፈታ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከብሩ የሚጠይቁ ግፊቶች ከየአቅጣጫው እየቀጠሉ መሆናቸው ይታወቃል።



