Holand Car PLC's Abay carEthiopia Zare (ሐሙስ ሚያዝያ 21 ቀን 2002 ዓ.ም. April 30, 2010)፦ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቤት መኪና በመገጣጠም የሚታወቀውና ”ሆላንድ ካር” የተሰኘው ኃ.የተ.ኩባንያ፤ ሁለት አይነት የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችን ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ። አንደኛው 130 ሰዎች የሚጭን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ባለአንድ ፎቅና 240 ሰዎችን የሚጭን መሆኑን አስታውቋል።

 

አውቶቡሶቹ የሚመረቱት በኦሮሚያ ክልል በቡራዩ አካባቢ ሲሆን፣ ሆላንድ ካር አውቶቡሶቹን ለማምረት በ30 ሚሊዮን ብር ካፒታል እንደሚንቀሳቀስ አስታውቋል።

 

በመጪው የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት (2003 ዓ.ም.) መስከረም ወር ላይ 130 ሰዎችን የሚጭነውን የመጀመሪያውን አውቶቡስ ይሠራል። ሆላንድ ካር አውቶቡሶቹን ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ወደፊት ለተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በመሸጥ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት ማቀዱን አስታውቋል።

 

ሆላንድ ካር በሀገር ውስጥ ”አባይ”፣ ”ተከዜ”፣ ”ሸበሌ” እና ”አዋሽ” የተሰኙ መኪኖችን በመገጣጠም የሚታወቅ ሲሆን፣ ድርጅቱ 230 ቋሚ ሠራተኞች አሉትና በቀን ከአምስት እስከ አስር መኪኖችን ያመርታል። አውቶቡሶቹን ማምረት ሲጀምር ደግሞ ለተጨማሪ 400 ሠራተኞች ቋሚ የሥራ ዕድል እንደሚከፍት ታውቋል።

 

ዘመናዊ አውቶቡሶች ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ ነጥብ ሦስት እስከ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ሲሆን፣ ሆላንድ ካር የሚያመርታቸውን አውቶቡሶች 800 ሺህ የኢትዮጵያ ብር ይሸጣቸዋል።

 

ሆላንድ ካር፤ ሆላንድ (ኔዘርላንድ) ሀገር የአውቶቡሶቹን ዲዛይን ያሠራ ሲሆን፣ አውቶቡሶቹ እንደጭነት መኪና ተሳቢ በከባድ መኪኖች ላይ የሚገጠሙና ከተሸካሚው መኪና ላይም በቀላሉ ሊነጠሉ የሚችሉ መሆናቸው ታውቋል። ሆላንድ ካር በሁለት ዓመት ውስጥም የመኪና መለዋወጫዎችን በሀገር ውስጥ ለማምረት ዕቅድ መያዙንና ከገጣጣሚነት ወደ አምራችነት ለማደግ ማቀዱ ታውቋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ