ጀርመን ራዲዮ በኢትዮጵያ እንዳይሰማ ታገደ
አራት ወጣት ሴቶች ታስረው ተፈቱ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ግንቦት 14 ቀን 2002 ዓ.ም. May 22, 2010)፦ ከትላንት አርብ ግንቦት 13 ጀምሮ የጀርመን ድምጽ ራዲዮ በኢትኦጵያ እንዳይሰማ መደረጉን የአዲስ አበባ ምንጮች በተለያዩ ቦታወች በመዘዋወር አረጋገጡ።
እንደምንጮቻችን ጥቆማ በጣቢያው ምንም አይነት ድምጽ እንደማይሰማና ይህ ሆነውም የመድረኩ ሊቀመንበር ዶ/ር በየነ ጴጥሮስ ስለ አውሮፓ ህብረት ታዛቢዎች እንቅስቃሴና ተግባር በሚመለከት የሰጡትን ወቅታዊ ሪፖርት ያቀርባሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት መሆኑን ለመረዳት ችለናል። ዶ/ር በየነ በተደጋጋሚ ታዛቢዎቹን ሲወቅሱ መሰማታቸው አይዘነጋም።
በተያያዘ ዜና ቅዳሜ ግንቦት 14 ቀን 2002 ዓ.ም ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት አካባቢ የፌደራሉ ፖሊስ ባልደረቦች የሆኑ የማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ቡድን አባላት በጽሕፈት እና በፎቶ ኮፒ አገልግሎት መስጠት ተግባር ላይ የተሰማሩ አራት ኢትዮጵያዊያትን ለምርመራ ከወሰደ በኋላ ከቀኑ 11፡40 ሰዓት ላይ መልሶ ለቋቸዋል። በጽህፈት እና በፎቶ ኮፒ አገልግሎት ስራ ላይ የተሰማሩት ኢትዮጵያዊያቱ ሰብለ፣መታሰቢያ፣ገነት እና አንድ ለጊዜው ስስሟ ያልታወቀ ሴት ናቸው። አራቱ ወጣት ሴቶች 6ኪሎ ዩንቨርስቲ 5ኛ በር ፊት ለፊት ከሚገኘው የአገልግሎት መስጫ አካባቢ ነበር በፖሊሶች የተወሰዱት። ፖሊስ ‹‹ጸረ-ሰላም የሆኑ ወረቀቶችን ፣ አባዝታችኋል፣ አከፋፍላች ል። ››በሚል ምክንያት ነበረ ለምርመራ የጠራቸው ። ይሁን እንጂ ‹‹ወጣቶቹ ሴቶች ህጋዊ በሆነ መልኩ በርካታ የተቃዋሚዎችን የምረጡኝ የቅስቀሳ ጽሁፎች ሲተይቡና ተለጣፊ ወረቀቶችን በፎቶ ኮፒ ሲያባዙ የቆዩ በመሆናቸውና በአካባቢው የተቃዋሚዎች ጽ/ቤት በመኖሩ ፖሊስ ይሄን ምክንያት አድርጎ እንዳሰራቸው ተገልጿል።
የኢህአዴግ መንግስት የ2002ዓ.ም ምርጫ ቅስቀሳ ከተጀመረ ወዲህ በተለያዩ ጋዜጠኞች፣ ራዲዮኖችና የህትመት አገልግሎት ሰጭዎች ላይ ከፍተኛ ወከባና እገዳ ሲያደርግ እንደነበር ተዘግቧል።



