በ3 ቋንቋዎች የተዘጋጁት ዲቪዲዎችግንቦት 7 2002 ዓ.ም. በለንደን ከተማ በኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሴንተር ሦስት የአማርኛ እና የኢትዮጵያ ዕሴቶች ማስተማሪያ ዲቪዲ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵውያን እና አፍቃሪ ኢትዮጵያውያን በተገኙብት በደማቅ ሁኔታ ተመረቀ።

 

አዘጋጁ ኢንጂንየር በላቸው ጨከነ ኢትዮጵያውያን ባህላቸውን፣ ታሪካቸውን፣ ቋንቋቸውን ለመጠበቅ ብሎም ለልጆቻቸው ለማስተማር ጉጉ እንደሆኑ፤ ነገር ግን አሁን በስደት በሚኖሩበት ሀገር የቴክኖሎጂ ዕድገት ደረጃ የሚመጥን ለልጆቻቸው ቋንቋቸውን ባህላቸውን እና ሀገራቸውን ለማስተዋወቅ በቂ ዘመናዊ መረጃዎች እንደሌላቸው አስረድተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ልጆች በምዕራቡ የመገናኛ ብዙኀን የሚያዩዋቸው፣ የሚሰሟቸው፣ የሚያነቧቸው፤ የኢትዮጵያን ችግር፣ ረሃብ፣ ጦርነት የሚያጎላ በመሆኑ፤ ልጆቹ በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው አመለካከት በጣም የተዛባ እንደሚያደርገው ካስረዱ በኋላ፤ ይህም ይህን ሥራ ለመሥራት እንዳነሳሳቸው በመክፈቻ ንግግራቸው ጠቁመዋል።

 

ለእንግሊዝኛ፣ ለጀርመንኛ እና ለፈረንሣይኛ ተናጋሪዎች የተዘጋጁት ዲቪዲዎች 
ለእንግሊዝኛ፣ ለጀርመንኛ እና ለፈረንሣይኛ ተናጋሪዎች የተዘጋጁት ዲቪዲዎች
ዲቪዲዎቹ ሦስት ዓይነት ሲሆኑ፤ ለእንግሊዘኛ፣ ለጀርመንኛ እና ለፈረንሣይኛ ተናጋሪዎች የተዘጋጁ ናቸው። ሦስቱም ዲቪዲዎች በይዘት አንድ ሲሆኑ፣ ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎችን ይዘዋል። የመጀመሪያው ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያን ታሪካዊ ሀብትና ባህል አውቀው ለኢትዮጵያ ያላችውን ግንዛቤ ማሳድግ ነው። ሁለተኛው የኢትዮጵያውያን የሆነውን የአማርኛ ፊደላት፣ የኢትዮጵያን ቁጥሮችን እና ቋንቋ በዘመናዊ መልኩ ማስተማር ሲሆኑ፤ ውጤቱም ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ወደፊት ለሀገራቸው ኢትዮጵያ ፍቅር እንዲያድርባቸው እና ባዕድ እንዳይሆኑ፤ ባህላቸውን እና ታሪካቸውን በራሳቸው ቋንቋ እንዲያውቁ፤ ከቤተሰባቸው ጋር ጤናማ ግንኙነት እንዲኖራቸው፤ ወደፊት በኢትዮጵያ በምርምር፣ በንግድ ሥራ እና በዲፕሎማቲክ ግንኙነቶች ረገድ እንዲሳተፉ እንደሚረዳቸው የኢትዮአምሃሪክ ድረገጽ ይጠቁማል።

 

በአጠቃላይ በዲቪዲው ውስጥ ከ10 የሚበልጡ ኢትዮጵያን በዓለም ልዩ የሚያደርጋት እሴቶች፤ 33ቱን የአማርኛ ፊደላት ከ400 በላይ ቃላት ከአቻ እንግሊዝኛ፣ ጀርመንኛ እና ፈረንሣይኛ ቃላት ጋር በስዕል ትደግፈው፤ ከሰባት በላይ በኢትዮጵያ በድምቀት የሚከበሩ በዓላት፣ የኢትዮጵያ ቁጥሮችን፣ ለልጆች ማረፍያ እንዲሆናቸው መዝሙርና ጨዋታዎች ተካተዋል። የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የፊደሉም ምንጭ ጠብቃም ያቆየችው እንደመሆኗ መጠን እና ለኢትዮጵያ ባለፉት ዘመናት ካደረገችው አስተዋጽዖ አንጻር በዲቪዲው ውስጥ የተወሰነ ሽፋን ተሰጥቷል።

 

የዲቪዲው ዋና አዘጋጅ ኢንጂንየር በላቸው ጨከነ ከሁለት ህጻናት ጋር በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ  
የዲቪዲው ዋና አዘጋጅ ኢንጂንየር በላቸው ጨከነ ከሁለት ህጻናት ጋር በምረቃው ሥነ-ሥርዓት ላይ
ኢንጂንየር በላቸው “በዚህ ዲቪዲ ዝግጅት 25 ሰዎች በቀጥታ፣ ከ50 በላይ ሰዎች በተዘዋዋሪ የተሳተፉ ሲሆን፣ ሥራው በአጠቃላይ ከሁለት ዓመት በላይ ፈጅቷል። በመጀመሪያ የተለያዩ የኮምፒዩተር ሶፍትዌሮችን በመጠቀም የአማርኛ መማሪያው የተዘጋጀ ሲሆን፤ የአማርኛን ቋንቋ ለመማር፣ የኢትዮጵያን ታሪክ ለማወቅ በማንኛውም ዕድሜ ክልል ያለ ሰው ሊጠቀምበት እንደሚችል እምነቴ ነው። ቋንቋን እና ባህር የሆነውን የኢትዮጵያን ታሪክ በአንድ ዲቪድ ማጠቃለል ፈጽሞ የማይታሰብ ሲሆን፤ ይህ ዲቪዲ ለወላጆች መነሻ እንዲሆናቸው እና ለሌሎች ባለሙያዎች በዚሁ ቀጥለውበት ወደፊት ብዙ ኢትዮጵያውያን የሚማሩበት የተሻሉ ሥራዎች እንደሚሠሩ ምኞቴ ነው” ሲሉ ገልጻዋል።

 

በመክፈቻው ላይ ንግግር ያደረጉት ወ/ሮ ፀሐይ አለማየሁ በዚህ በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላሉ ልጆች ባህላችንና ቋንቋችንን ለማስተማር እንደዚህ ያሉ የሙያ ምርቶች አስፈላጊ እንደሆኑ አውስተው፤ የሚዘጋጁት መርጃዎች ዕለት ዕለት ልጆች ከሚጠቀሙባቸው መማሪያዎች በጥራትም በብዛትም ደረጃ ተቀራርበው መዘጋጀት እንደሚገባቸው ገልጸዋል። ይህም የተሠራው ሥራ አንዱ እንደሆነ አውስተዋል።

 

በመክፈቻው ላይ ከነበሩት እንግዶች አንዱ “በተማርነው ሙያ ሀገርንና ወገንን የሚጠቅም ነገር ካልሠራንበት ድግሪ፣ ማስተር፣ ፒ.ኤች.ዲ. መያዝ ምንም አይጠቅምም። በሙያችን የሚዳሰስ የሚታይ ነገር መሥራት አለብን።” በማለት ይህንን ሥራ የሠሩትን ባለሙያዎች አድንቀው፤ የተሠራው ሥራ ብዙ የተደከመበት እና ለወቅቱ ችግር መፍትሔ የሚሰጥ ወቅታዊ ሥራ ነው ብለዋል።

 

ኢትዮጵያ ከዓለም መጀመሪያ ፊደልን ከቀረጹ ጥቂት ሀገሮች አንዷ ስትሆን፤ ከወረቀት በፊት በብራና፣ ከብራናም በፊት በድንጋይ ኢትዮጵያውያን ሃሳባቸውን ይገልጹ እንደነበር የዘርፉ ተመራማሪዎች ያስረዳሉ። ዛሬም ኢትዮጵውያን ለሥራም ሆነ ለአምልኮት እግዚእብሔር የራሳቸው የሆነውን የግዕዝ ፊደል የሚጠቀሙ ሲሆን፤ በእንደዚህም ፊደላት የተጻፉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ መጻሕፍት በኢትዮጵያ እና በዓለም ቤተመጻሕፍት ይገኛሉ። ኢትዮጵያውያን ሃሳባቸውን በጹሑፍ መግለጫ ከሆነው ፊደል በተጨማሪ ዓለምን የሚያስደንቁ ታሪካዊ ጥበባት፣ ባህል፣ ልዩ የሆነ የምድር አቀማመጥ እና እምቅ የሆኑ ሀብቶች ባለቤት መሆናቸው ይታወቃሉ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ