አንድነት ፓርቲ ከ6 ሺህ በላይ ፊርማ አሰባሰበ
Ethiopia Zare (ኀሙስ ሚያዝያ 2 ቀን 2000 ዓ.ም. April 10,2008)፦ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ለማቋቋም የሚንቀሳቀሰውና በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው ቡድን ከስድስት ሺህ በላይ ፊርማ አንዳሰባሰበ ለፓርቲው ቅርብ የሆኑ ምንጮች ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ገለጡ።
የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕግ አንድ ፓርቲን ለማቋቋም ከአራት የተለያዩ ክልሎች አንድ ሺህ አምስት መቶ ፊርማ ማሰባሰብ እንደሚገባው መደንገጉ ይታወቃል። የአንድነት ፓርቲም ይህንኑ መስፈርት ለማሟላት በተለያዩ ክልሎች አባላቱን አሰማርቶ እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም።
በተለያዩ ክልሎች ፊርማ ለማሰባሰብ ተሰማርተው የነበሩት ቡድኖች ሲመለሱ በዚህ ሣምንት ብቻ በጠቅላላው ከስድስት ሺህ በላይ ፊርማ እንደተሰበሰበ ለመወቅ ተችሏል። ፓርቲው በቀጣዩ ሂደት ላይ እየተነጋገረ እንደሆነና ፓርቲውን ሕጋዊ ፈቃድ ለማሰጠት የሚያስችለውን ዝግጅት እያገባደደ እንደሆነ ታውቋል።



