Ethiopia Zare (ሰኞ ግንቦት 23 ቀን 2002 ዓ.ም. May 31, 2010)፦ የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በግንቦት 15 ቀን 2002 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ለተካሄደው ምርጫ ውዝግብ፤ ድጋሚ ምርጫ መፍትሔ ሊሆን እንደማይችል በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ ገለጸ።

 

 

የኢዴፓ ከፍተኛ አመራር አባላት በየምርጫ ጣቢያዎች ለቅስቀሳ ከአዲስ አበባ ውጭ በመውጣታቸው እስኪሰባሰቡ ድረስ መግለጫ ከመስጠት እንደተቆጠበ የተገለጸ ሲሆን፤ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አቶ ልደቱ አያሌው፣ አቶ ሙሸ ሰሙና የድርጅት ጉዳይ ኃላፊው አቶ መስፍን መንግሥቱ ተገኝተው ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።

ድጋሚ ምርጫን በሚመለከት የተጠየቁት አቶ ልደቱ አያሌው ድጋሚ ምርጫ ማድረግ በምርጫው የተከሰቱትን ችግሮች በእጥፍ የሚጨምር እንጂ ፍትሃዊነትን አያስገኝም፤ ችግሩን መፍታት የሚቻለው የተቋማት ችግሮች ላይ መፍትሔ ለማምጣት ገዥው ፓርቲ ከተቃዋሚዎች ጋር መደራደር ሲችል ነው ብለዋል።

 

በምርጫው 31 ችግሮች እንደነበሩበት በዝርዝር ያስቀመጠው የኢዴፓ መግለጫ፤ መደረግ አለባቸው ያላቸውን ባለ ስድስት ነጥብ መቋጫ ሃሳቦች አስቀምጧል።

 

የኢዴፓው ሊቀመንበር የምርጫ 2002 ውጤት የሠላማዊ ትግሉን ሂደት 19 ዓመት ወደኋላ መመለሱንና በትጥቅ ትግል የሚያምኑ ኃይላትን በእጅጉ የሚያጠናክር እንደሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

 

ገዥው ፓርቲ ከ96 በመቶ በላይ አሸንፌያለሁ ያለበትን ‘ምርጫ’ ስምንት የተለያዩ ፓርቲዎችን ያቀፈው መድረክና በኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል የሚመራው መኢአድ ድጋሚ እንዲደረግ መጠየቃቸው ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ