Ethiopia Zare (ዓርብ ሚያዝያ 3 ቀን 2000 ዓ.ም. April 11,2008) የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፌዴራል ከፍተኛና የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አስተዳደር ዳይሬክተሩ አቶ ዳኛቸው ካሣ በሠራተኞች በቀረበባቸው አቤቱታ መሠረት ጉዳዩን እንዲያጣራ የተቋቋመው ኮሚቴ ያቀረበውን ሪፖርትና የዳኞች አስተዳደር ጉባዔ የደረሰበትን በሚመለከት ለመነጋገር በዛሬው ዕለት ከሰዓት በኋላ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ስብሰባ መጠራቱን ለማወቅ ተችሏል።

 

ምንጮች እንደጠቆሙት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አስተዳደር ዳይሬክተር አቶ ዳኛቸው ካሣ ሠራተኞችን በድለዋል በሚል የቀረበባቸውን አቤቱታ አስመልክቶ፣ ገለልተኛ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን ያጣራ ሲሆን፣ አጣርቻለሁ ያለውን ሪፖርቱ ለዳኞች አስተዳደር ጉባዔና ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ለአቶ ከማል በድሪ ማቅረቡን መዘገባችን ይታወሳል።

 

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ አቶ አማረ ሙሄ፣ አቶ መድኅን ኪሮስ እና ወይዘሮ ዘነበች ክስቴ የተባሉ ዳኞች በአጠቃላይ አራት አባላት ያሉት ኮሚቴ መቋቋሙንና ይህም ኮሚቴ ሪፖርት ማቅረቡ ይታወቃል።

 

የኮሚቴው ሪፖርት ለጉባዔውና ለፕሬዝዳንቱ ከቀረበ አንድ ወር የሆነው ቢሆንም እስካሁን የተሰጠ መልስ ያልነበረ ሲሆን፣ በዛሬው ዕለት በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ወደ 150 የሚጠጉት የፌዴራል ፍርድ ቤት ዳኞች፤ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ግቢ ከሰዓት በኋላ እንዲገኙ ጥሪ ተደርጎላቸዋል።

 

በአራት አባላት የተቋቋመው ኮሚቴ ሪፖርት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አስተዳደር ዳይሬክተሩ በስድስት ሴቶች ላይ ጾታዊ ትንኮሳ ፈጽመዋል፣ በርካታ ገንዘብ ተመዝብሯል፣ ከ50 በላይ የቅርብ ቤተሰቦቻቸውን ቀጥረዋል የሚል ይዘት ያለው እንደሆነ መዘገባችን ይታወሳል። ይህንን አስቸኳይ ስብሰባ ለመጥራት ባለፈው ሣምንት በእንቢልታ ጋዜጣ የተጋለጠውና በኢትዮጵያ ዛሬ አማካኝነት ለመላው ዓለም የተነበበው ዘገባ ለህዝብ ከቀረበ በኋላ ጉዳዩን ምስጢር አድርጎ ማቆየት አስፈላጊ ሆኖ አለመገኘቱን ጉዳዩን የያዙት የኢህአዴግ ባለሥልጣናት በማመናቸው መሆኑን ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ።

 

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንጋፋ ጋዜጠኛ "ዘገባው ልቅም ተደርጎ የተሠራና የፕሬስ አስፈላጊነትን አጉልቶ የሚያሳይ፣ እንዲሁም የሀገሪቱ ባለሥልጣናት በህዝብ ላይ ለረጅም ዓመታት በግልጽ እየታወቁ ምን አይነት አሰቃቂ ድርጊት እንደሚፈጽሙ ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነው" ሲሉ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ