Ethiopia Zare (ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2002 ዓ.ም. June 21, 2010)፦ በአዲስ አበባ ከአራት ኪሎ ጀምሮ እስከ ሁለተኛ ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ ያሉ ቤቶች እንዲፈርሱ ተወስኖ፤ መሬቱ ለግል ባለሀብቶች መሸጡ ታወቀ። ተፈናቃዮቹ ከአቅማቸው በላይ ገንዘብ ከፍለው ኮንደሚንየም ቤቶች ውስጥ እንዲገቡ ተጠየቁ።

 

መንግሥት መሬቱን ሲሸጥ በአካባቢው በቀበሌም ይሁን በኪቤአድ ቤት ተከራይተው ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች ተለዋጭ ቤት የመሥጠት ግዴታ አለበት። ይሁን እንጂ ”ፉሪ” የተባለ አካባቢ መንግሥት ወዳስገነባው ኮንደሚንየም ቤቶች የሚፈናቀሉት ነዋሪዎች እንዲገቡ ተነግሯቸዋል። ለዚህም ተፈናቃዮቹ ቅድሚያ ክፍያ 20 ሺህ ብር ተጠይቀዋል።

 

ባለሁለት መኝታ ቤት ኮንደሚንየም ውስጥ ለሚገባ ሃያ ሺህ ብር፣ ባለአንድ መኝታ ቤት ውስጥ ለሚገባ ደግሞ አስር ሺህ ብር ቅድሚያ ክፍያ እንዲከፍሉ ተነግሯቸዋል። በዚህም ምክንያት በርካቶቹ የአካባቢው ነዋሪዎች የተጠየቁትን ክፍያ የመክፈል አቅም ስለሌላቸው ከፍተኛ ጭንቅ ውስጥ መሆናቸውን ለመረዳት ችለናል።

 

የተጠየቁትን ገንዘብ ፈፅሞ ማግኘትም ሆነ መክፈል አንችልም ያሉ ወገኖች ደግሞ፤ በከተማይቱ በሚገኙ አንዳንድ መንግሥታዊ መጋዘኖች ውስጥ መቀመጥ እንደሚችሉ ተገልፆላቸዋል።

 

ይህ የመንግሥት ውሳኔ ተግባራዊ የሚሆነው ከሰኔ 30 ቀን እስከ ሐምሌ 15 ሲሆን፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ይህን መሰል እርምጃ ሲወሰድ ቢያንስ የአንድ ዓመት የዝግጅት ጊዜ መሰጠት ነበረበት ሲሉ እርምጃው ተገቢና ኢ-ሰብዓዊነት የጎደው ነው በማለት ድርጊቱን ኮንነዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ