ኢትዮጵያዊያን በቶሮንቶ መለስን ተቃውመው ለመሰለፍ እየተሰናዱ ነው
ከዋሽንግተን ዲሲና ከቫንኩቨር ድረስ ኢትዮጵያዊያን እየገቡ ነው
ተክለሚካኤል አበበ-ከቶሮንቶ
እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠርኸ ከጁን 26 እስከ ጁን 27 በሚካሄደው የጂ 20 ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ ይመጣል ተብሎ የሚጠበቀውን አቶ መለስ ዜናዊና ተከታዮቹን ለመቃወም ከፍተኛ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንና ከሰሜን አሜሪካ የተለያዩ ከተሞች አያሌ ኢትዮጵያዊያን ወደ ቶሮንቶ ይገባሉ ብለው እንደሚጠብቁ አዘጋጆቹ ገለጹ።
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስተር የወቅቱን የአፍሪካ አንድነት ሰብሳቢ የማላዊውን ፕሬዚዳንትና ኢትዮጵያን የጋበዙ ሲሆን እንደተለመደው አምባገነኑ መለስ ዜናዊ በዚህ ስብሰባ ላይ ይገኛል። ስብሰባውን እንዳይካፈልና ወደ ካናዳ የመግቢያ ፈቃድ እንዳይሰጠው በካናዳ በሚኖሩ የተለያዮ የሰበአዊ መብት ተሟጋቾች የተጠየቀበት አቶ መለስ ስብሰባውን ለመካፈል ቶሮንቶ መግባቱ የታወቀ ሲሆን ኢትዮጵያዊያን ካናዲያዊያኖቹ ካናዳም ትሁን ሌሎች ዴሞክራሲያዊ አገሮች እንደ መለስ ያሉ አምባገነን መሪዎችን ማስጠጋት የለባቸውም የሚል መልእክት ለማስተላለፍና በኢትዮጵያ ውስጥ እደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብት ገፈፋና አፈና ለመቃወም ሰልፉ መዘጋጀቱን አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
የካናዳ መንግስት አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚፈጀውን ስብሰባ ለማዘጋጀት መሰናዳት ከጀመረበትና ለመለስ ዜናዊ ግብዣውን ከላከበት ጊዜ ጀምሮ በካናዳ የሚገኙ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የአቶ መለስን በዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠርጣሪነት በመጥቀስ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ሰንብተዋል።
በስብሰባው ፕሮግራም መሰረት የስብሰባው ተሳታፊ መሪዎች ቅዳሜ ጠቅለው እንደሚገቡና የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስተር ሰቲፈን ሀርፐርና ባለቤቱ ቅዳሜ ማታ የአቀባበል ግብዣ እንደሚያደርጉላቸው የታወቀ ሲሆን፡ ዋናው ስብሰባ እሁድ እለት በሜትሮ ቶሮንቶ የጉባኤ ማእከል እንደሚካሄድ ታውቋል።
በቶሮንቶና አካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ቅዳሜ ጁን 26 ቀን ከጠዋቱ 9ሰዓት ጀምሮ በክዊንስ ፓርክ የሚደረገውን ከፍተኛ ተቃውሞ ሰልፍ ጨምሮ፡ በእለቱ ከምሽቱ 7 ሰዓት ጀምሮ የካናዳ ፓርላማ አባላት ይገኛሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ዶናልድ ጎዳና ገቢው ለሰብአዊ ተሟጋች ድርጅቶችና የነጻው ፕሬስ አባላት የሚሆን የራት ዝግጅት እንዳዘጋጁም ታውቋል።
በዋሽንግተን ዲሲ የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆነው ዶ/ር ካሳ በአካባቢው የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለቶሮንቶ አካባቢ ኢትዮጵያዊያን አጋርነታቸውን ለመግለጽና ለመለስ ያላቸውን ተቃውሞ ለማሳየት በአውቶብስ ከዲሲ እንደሚጓዙና የቶሮንቶውን ተቃውሞ እንደሚቀላቀሉ ገልጾዋል።
ከካናዳ ምእራብ ጫፍ ቫንኩቨርን ጨምሮ ከኪችነር፣ ከሎንዶን፣ ኦታዋና ሌሎች የአካባቢው ከተሞችም ብዙ ሰዎች ለተቃውሞ ሰልፉ እንደሚመጡ ታውቋል።



