በዩጋንዳ-ካምፓላ ሁለት ፈንጂዎች ፈንድተው ከ64 በላይ ሰዎች ሞቱ
አንዱ ፈንጂ በኢትዮጵያዊያን ሬስቶራንት ውስጥ ፈንድቷል
Ethiopia Zare (እሁድ ሐምሌ 4 ቀን 2002 ዓ.ም. July 11, 2010)፦ በዩጋናዳዋ መናገሻ ካምፓላ ራግቢ ክለብ በተባለ ቦታና የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ውድድርን ለመከታተል በአንድ የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ውስጥ በተሰባሰቡ ሰዎች መሀል በፈነዱ ሁለት ፈንጂዎች ምክንያት በርካታ ኢትዮጵያኖችን ጨምሮ 64 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ።
በፍንዳታው የተጠቁ ቁጥራቸው ያልታወቀ ከባድና ቀላል ቁስለኞች ሲኖሩበት፣ አንድ አሜሪካዊም በጥቃቱ መሞቱ ተጠቁሟል። የሶማሊያው አል ሻባብ እጁ ሊኖርበት እንደሚችል ጥቆማዎች ቢኖሩም ይህ ዜና እስከተጠናከበረበት ጊዜ ድረስ ማንም ተቋም ኃላፊነቱን የወሰደ እንደሌለ ለማወቅ ተችሏል።
አንድ ሶማሊያዊ መልክ ያለው ከአንገት በላይ አካል ማግኘታቸውን የገለጹት የዩጋንዳ ፖሊሶች፤ ምናልባት ይህ ሰው አጥፍቶ ጠፊ ሊሆን ይችላል የሚል ጣርጣሬ ላይ እንዳሳደረባቸው ጠቁመዋል። ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ስለሁኔታው ምንም አይነት መረጃ ለመስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል።
በካምፓላ ለደረሰው ጥቃት የአል ሻባቡ ሸክ ዩሱፍ ሸህ አይዛ ድርጅታቸው ከጥቃቱ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደሌለው ገልጸው፤ “ዩጋንዳ ከጠላቶቻችን አንዷ ናት ጠላቶቻችን በሚያጋጥሟቸው ማናቸውም ኀዘን እኛ እንደሰታለን” ብለዋል።
የኢትዮጵያ ጦር ከሶማሊያ በአስገዳጅ ሁኔታ ከወጣ በኋላ አል ሸባብ 5ሺህ የሚደርሱትና ከዩጋንዳና ከቡሩንዲ የተውጣጡት የአፍሪካ ህብረት ጦር ከሞቃዲሾ በአስቸኳይ እንዲወጣ በአጽንዖ ሲጠይቅ እንደነበርና ማስፈራሪያዎችንም ሲሰነዝር መቆየቱ አይዘነጋም።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ በድርጊቱ በእጅጉ ማዘናቸውን ገልጸው፤ ለሟቾቹ ቤተሰቦች የተሰማቸውን ጥልቅ ኀዘን ከመግለጻቸውም በላይ መንግሥታቸው የዩጋንዳ መንግሥት በሚጠይቃቸው ማናቸውም እርዳታ ለመተባበር ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያው አገዛዝ በሶማሊያ ምድር ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት አሰማርቶ እንደነበርና በ2009 እ.ኤ.አ. መጨረሻ ጦሩን ከሶማሊያ ምድር ማስወጣቱ የሚታወቅ ሲሆን፤ በዚህ ድርጊት ያልተደሰቱ በርካታ ሶማሊያውያን በኢትዮጵያ ላይ ጥላቻ እንደቋጠሩ ይታወቃል።
አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች በዩጋንዳው የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ላይ የደረሰው ጥቃት የዚሁ እርምጃ በቀል ነው ሲሉ ተደምጠዋል።



