L.Colonel Mengistu H.Mariamበዛሬው ዕለት ገበያ ላይ የዋለው ሁለት ሺህ ቅጂ በአንድ ሰዓት ውስጥ አለቀ

Ethiopia Zare (ዓርብ ሐምሌ 16 ቀን 2002 ዓ.ም. July 23, 2010)፦ በጋዜጠኛና ፀሐፊ ገነት አየለ የተዘጋጀው ”የሌተና ኰሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትዝታዎች (ቁጥር 2)” መጽሐፍ ነገ ቅዳሜ ሐምሌ 17 ቀን 2002 ዓ.ም. (ጁላይ 24 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.) በኦፊሴል ገበያ ላይ ይውላል። ዛሬ ማምሻውን በጥቂቱ ለሽያጭ የቀረበው ሁለት ሺህ ቅጂ በአንድ ሰዓት ውስጥ ተሸጦ ማለቁን ከአዲስ አበባ የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ሪፖርተር ዘግቧል።

 

የዚህ መጽሐፍ ቁጥር አንድ በ1994 ዓ.ም (2002 እ.ኤ.አ.) ለመጀመሪያ ጊዜ በሜጋ አሣታሚ ታትሞ የነበረ ሲሆን፣ በዚህ በያዝነው ዓመት ለአራተኛ ጊዜ ቁጥር አንድ መጽሐፉን አስር ሺህ ቅጂ ያሣተመው የግል አሣታሚ (ክቡር አሣታሚ) ”ቁጥር ሁለት” መጽሐፉን ማሣተሙን ለማወቅ ችለናል።

 

የመጽሐፉ ዋጋ

ይኸው ”የሌ/ኰ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ትዝታዎች” የተሰኘው ቁጥር ሁለት መጽሐጽ ባለ 200 ገጽ ሲሆን፣ የመጽሐፉ የመሸጫ ዋጋ የኢትዮጵያ ብር 35 መሆኑን ለመረዳት ችለናል። በዛሬው ዕለት ማምሻውን ከምሽቱ አስራ አንድ ሰዓት ተኩል ላይ ለገበያ የተለቀቀውን ሁለት ሺህ ቅጂ በፍጥነት ማለቅ የተመለከቱ የመጽሐፍ አፍቃሪዎች፤ የመጽሐፉ ዋጋ በነጋዴዎችና በቸርቻሪዎች ሊያሻቅብ እንደሚችል ያላቸውን ግምት ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ገልጸዋል።

 

የመጽሐፉ ዋጋ በኢትዮጵያ እየታተሙ ካሉት መጻሕፍት ጋር ሲወዳደር እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን የገለጹት የመጽሐፍ አፍቃሪዎች በምሣሌነት በዚህ በያዝነው ዓመት ታትመው ለገበያ የቀረቡትን መጻሕፍት ጠቅሰዋል። ከነዚህም ውስጥ የፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም ”አገቱኒ” የተሰኘውና በቅርቡ የወጣው መጽሐፍ የኦፊሴል የመሸጫ ዋጋ ብር 50 መሆኑን እና የአቶ ልደቱ አያሌው ”መድሎት” የተሰኘው መጽሐፍ ደግሞ በኦፊሴል በብር 60 መሸጡን ጠቅሰዋል።

 

የመጽሐፉ ይዘት

የሌ/ኰ መንግሥቱ ትዝታዎች ቁጥር ሁለት መጽሐፍ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ፕ/ት ሌ/ኰ መንግሥቱ ውጪ የተለያዩ የደርግ ወታደራዊ ባለሥልጣናት፣ ጄኔራሎች፣ ... እንዲሁም የመንግሥት ባለሥልጣናት የደርግን ሥርዓት አስመልክተው የልባቸውን እንደሚናገሩበትና እንደሚናዘዙበት ታውቋል። ከእነዚህም ውስጥ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ አንዱ መሆናቸውን ለመረዳት ችለናል።

 

በቁጥር ሁለት መጽሐፉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ጓዶች፣ ጄኔራሎች እና የጦር መኮንኖች እንደ ቁጥር አንዱ ሁሉ በስማቸው ፈንታ በቁጥር ነው የሚጠሩት። ለምሳሌ ”ጓድ ቁጥር 90” በሚል የሚጠሩት ጓድ፤ የመጀመሪያውንና ቁጥር አንድ መጽሐፍን በመልካምና በመጥፎም ሁኔታ በመተቸት ይጀምራሉ።

 

ጓድ ቁጥር 90 ከሚተቿቸውና ሃሳባቸውን ከሚገልጹባቸው ጉዳዮች ውስጥ፤ ሌ/ኰ መንግሥቱ ኃይለማሪያምን ማርክሲዝም ሌኒንዝም ብዙ ጊዜ ያስጠኗቸው የነበሩት ሰናይ ልኬ ሳይሆኑ ባሮ ቱምሳ እንደነበሩ ይገልጻሉ። ጓድ ቁጥር 90 ይህንን ጉዳይ ሲገልጹ፤ ”... ሰናይ ልኬ የማርክሲዝም ዕውቀቱ እንደነ ኃይሌ ፊዳ የጠለቀ አልነበረም። ትንሽ ጡንቸኛ ነኝ ይላል። ወታደሮቹን ማለትም የመንግሥቱን አጃቢዎች እየሰበሰበ ካራቴ ያስተምራል። እና በዚህ ጠጋ ጠጋ እያለ መንግሥቱን ለመቅረብ ቻለ እንጂ፤ በዕውቀት ሌሎቹ ይበልጡታል። ሰደድ ሲደራጅ ወዝ ሊግም ተደራጀ። የነዚህ ሁሉ የጋራ ስጋታቸው የመኢሶን መጠናከር ስለነበር ያ ይበልጥ ሰናይ ልኬን ከወታደሮቹ ጋር አቀራረበው። ...” በማለት በብዙኀን ዘንድ የታመነውንና በቁጥር አንድ መጽሐፍ ላይ የሰፈረውን ሃሳብ ይተቻሉ።

 

የአጻጻፍ ስልቱ

የመጽሐፉ አጻጻፍ ስልት ከቁጥር አንዱ ለየት ያለና የተሻለ መሆኑን መጽሐፉን ከሕትመት በፊት ያነበቡት ወገኖች ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጸዋል። ቁጥር አንድ መጽሐፉ በጥያቄና መልስ የቀረበ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር ሁለት መጽሐፉ ደግሞ በጉዞ ማስታወሻ መልክ የቀረበና በርዕሰ ጉዳዮች ተከፋፍሎ የተፃፈ መሆኑን ለመረዳት ችለናል። ከዚህም ሌላ በመጽሐፉ ከሌ/ኰ መንግሥቱ ባልተናነሰ ሁኔታ ሌሎች የደርግ ሥርዓት አባላት ሰፋ ያለ ድርሻ ተሰጥቷቸዋል።

 

በመጽሐፉ ላይ ያሰባሰብናቸው አስተያየቶች

”የሌ/ኰ መንግሥቱ ኃይለማሪያም ትዝታዎች - ቁጥር ሁለት” በሚል የታተመውን መጽሐፍ ቅድመ ሕትመት ቅጂ ካነበቡ ወገኖች ያሰባሰብናቸው መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ፤ መጽሐፉ በተለይም የደርግ ሥርዓትን አስመልክቶ እስከዛሬ ከተጻፉት መጻሕፍት ውስጥ ይሄ መጽሐፍ ሚዛናዊና ሙያዊ ሥነምግባሩን የጠበቀ እንደሆነ ገልጸውልናል። ከዚህም ሌላ ከቁጥር አንዱ በተሻለና አዳዲስ መረጃዎችን የሚያቀርብ ከመሆኑም በላይ፤ ለተመራማሪዎች በመረጃ ሰጪነቱም ሆነ በጠቋሚነቱ የበለጠ ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!