Mr. Jaan AlbrechtAto Girma WakeEthiopia Zare (ሐሙስ መስከረም 20 ቀን 2003 ዓ.ም. September 30, 2010)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ”ስታር አሊያንስ” የተሰኘውን ዓለም አቀፍ የአየር መንገዶች ሕብረት በሚቀጥሉት 12 ወራት ለመቀላቀል ረቡዕ መስከረም 19 ቀን 2003 ዓ.ም. ተፈራረመ። አየር መንገዱ ከግብፅ እና ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ ሕብረቱን ሲቀላቀል ሦስተኛው የአፍሪካ አየር መንገድ ይሆናል።

ስምምነቱን በሼራተን ሆቴል የተፈራረሙት በቅርቡ ሥልጣናቸውን የሚለቅቁት የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኦፊሠር አቶ ግርማ ዋቄ እና የስታር አሊያንስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃን አልብሬክት ናቸው።

 

”በስታር አሊያን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ቦርድ ስም የኢትዮጵያን አየር መንገድ ከስታር አሊያንስ ጋር እንዲሠራ ስምምነቱን መፈራረም ታላቅ ደስታን ሰጥቶኛል” ሲሉ ጃን አልብሬክት ተናግረዋል። አክለውም ”የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ያሉት የበረራ መስመሮች ለስታር አሊያንስ ተጓዦች በርካታ ምርጫዎችን ሲያስገኝ ለሕብረቱ ደግሞ አዲስ ገበያና ትርፍ ያስገኝለታል” ሲሉ ተናግረዋል።

 

ተሰናባቹ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኦፊሠር አቶ ግርማ ዋቄ በበኩላቸው ደግሞ፣ ”ኢትዮጵያ የስታር አሊያንስ ዓለም አቀፍ መረብ ተጠቃሚ እንድትሆን ያስችላታል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ገበያ ያለውን ልምድ፣ በአዲስ አበባ እና በሎሜ (ቶጎ) ያሉትን ሁለት ዋና ጣቢያዎች መሠረት ያደረጉት የበረራ መስመሮች የስታር አሊያንስ አባል አየር መንገዶች በአፍሪካ አዲስ ገበያ እንዲኖራቸው ያደርጋል።” በማለት ተናግረዋል።

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስታር አሊያንስ ሙሉ አባል የሚሆነው በሚቀጥሉት 12 ወራት ውስጥ መሆኑ ታውቋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከተለያዩ አየር መንገዶች ጋር በጋራ እንደሚሠራ ይታወቃል። ከእነዚህም ውስጥ ሳስ (ስካንዲኔቪያን ኤርላይንስ) እና ሉፍታንሳ ናቸው።

 

በአሁኑ ወቅት ስታር አሊያንስ የ28 አየር መንገዶች ሕብረት ሲሆን፣ እነርሱም ሉፍታንሳ፣ ሳስ (ስካንዲኔቪያን ኤርላይንስ)፣ ኤር ቻይና፣ ኤር ካናዳ፣ ኮንቲነንታል ኤርላይንስ፣ ኦስትሪያን፣ ኤር ኒውዚላንድ፣ ብሉዋን፣ ዩናይትድ፣ ተርኪሽ ኤርላይንስ፣ ክሮሺያ ኤርላይንስ፣ አድሪያ፣ አጌና፣ አና፣ የግብፅ አየር መንገድ (ኢጅብት ኤር)፣ የደቡብ አፍሪካ አየር መንገድ፣ ሲንጋፑር ኤርላይንስ፣ ስዊስ ኤርላይንስ፣ ታይ (የታይላንድ አየር መንገድ)፣ ዩ.ኤስ. ኤርዌይስ፣ ታፕ ፖርቹጋል፣ ስፓን ኤር፣ ፖሊሽ ኤርላይንስ፣ ኦስትሪያን፣ ብረስልስ ኤርላይንስ፣ ታም፣ ቢኤምአይ እና አሲያና ኤርላይንስ ናቸው።

 

ሕብረቱ 4 027 አውሮፕላኖች፣ 405 ሺህ ሠራተኞች፣ በዓመት 627 520 000 መንገደኞች፣ 1 172 አየር ማረፊያዎች፣ በቀን ከ21200 በላይ በረራዎችን በ181 ሀገሮች የሚያካሂድ ሲሆን በዓመት የሽያጭ ገቢው 156 ነጥብ 8 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መሆኑ ታውቋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ