ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንድትፈታ ለተሟገቱ ካናዳዊያን የምስጋና ዝግጅት ተሰናዳ
በተለይ ክቡር ሚስተር ፒተር ጁሊያንና ፓርቲያቸው አብዩን ሚና ተጫውተዋል
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ጥቅምት 6 ቀን 2003 ዓ.ም. October 16, 2010)፦ ብርቱካን ሚደቅሳ ከእስር እንድትፈታ የካናዳን ፓርላማ በመወትወት የሚታወቁትና የበርናቢ ኒውዌስት ሚኒስትር የኤን. ዲ. ፒ. ፓርቲ የፓርላማ ተመራጭ የሆኑት ክቡር ሚስተር ፒተር ጁሊያንንና አጋሮቻቸውን የሚያከብርና ለብርቱካን መፈታት ያደረጉትን አስተዋጽኦ የሚያደንቅ የምስጋና ስነስርአት በቫንኩቨር ነዋሪዎች መዘጋጀቱ ተገለጸ።
በካናዳ ብሄራዊ ሸንጎ ፓርላማ ወይንም በተለምዶ “ዘ ሃውስ ኦፍ ኮመን” በመባል ለሚታወቀው የካናዳ ፓርላማ የብርቱካን እስር በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብት ረገጣ የሚያሳይ ነው በማለት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወ/ት ብርቱካን እንድትፈታ ሞሽን 334 (M-334) እየተባለ የሚታወቀውን ያረቀቁትና ያቀረቡት ፒትር ጁሊያን ብርቱካን በመፈታቷ የተሰማቸውን ደስታ ለከተማው ነዋሪዎች በጻፉት ኢ-ሜይል አሳውቀው ነበር። አቶ ፒተር ጁሊያን ከሌሎች የካናዳ ፓርላማ ተመራጮች ጋር በመሆን፡ በካናዳ ሌሎች አካባቢዎችም ብርቱካን እንድትፈታ የሚጠይቅና ለካናዳ ፓርላማ የሚቀርብ የፊርማ ወረቀት እንዲፈረም በማድረግና በየግዜው በሚሰጧቸው ጠንካራ መግለጫዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የሰብአዊ መብት ረገጣና የፖለቲካ እስረኞች ሁኔታ ሲያጋልጡ ቆይተዋል።
ሚስተር ፒተር ጁሊያን በነሀሴ 28 በቫንኩቨር በተካሄደው የመጀመሪያው የኢትዮጵያዊያን የሳመር ፌስቲቫል ላይ “ብርቱካን ባስቸኳይ መፈታት አለባት” ብለው ሰውን የቀሰቀሰና ያነሳሳ ንግግር አድርገው ነበር።
ከ644 ቀናት እስራት በኋላ የብርቱካንን መፈታት ተከትሎ ነዋሪነታቸው በቫንኩቨርና አካባቢው የሆኑ ብርቱካን በእስር በነበረችበት ሰዓት አምስት ሺህ የካናዳ ገንዘብ አዋጥተው የላኩና በ2008/9 ብርቱካንን የአመቱ ታላቅ ሰው ብለው የሸለሟት ሴቶች ኢትዮጵያዊያን፣ ታላቅ የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆኑትን ፒተር ጁሊያንን ጨምሮ የበርናቢ ክፍለ ከተማን ከንቲባ ሚስተር ዴሪክ ኮሪገንን እንዲሁም የብሪቲሽ ኮሉምቢያ ክልል ተመራጭ ሚስተር ራጅ ችኋንንና የበርናቢ ከተማ ካውንስለር ፖል ማክዶናልድን የካናዳ መንግስት የብርቱካንን ጉዳይ አስመልክቶ እርምጃ እንዲወስድ ባደረጉት ያላሳለሰ ጥረትና በኢትዮጵያ እውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲሰፍን ያላቸውን ምኞት በማድነቅ የምስጋና እራት ግብዣና የሽልማት ስነስርአት ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ለማወቅ ችለናል።
አዘጋጆቹ የቫንኮቨር ነዋሪዎች በተለይ ሴቶች እህቶች እንደገለጹት የዝግጅቱ ዋና አላማ ለብርቱካን መፈታት ብቻ ሳይሆን ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱም ጥረታቸው የሚቀጥል መሆኑን ለመግለጽና በችግር ጊዜ የረዱንን የማናቸውንም ሀገር ዜጎች ማመስገን ተገቢ መሆኑን ስላመንበት ነው በማለት በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ የገለጹ ሲሆን በሌሎች ሀገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ይህንኑ አይነት እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ምክራቸውን ለግሰዋል።
በዚሁ በላሊበላ የኢትዮጵያ ሬስቶራንት ቅዳሜ October 16, 2010 ከምሽቱ 6pm ጀምሮ በሚካሄደው የራት ግብዣ ላይ የፓርላማው ተመራጭ ፒተር ጁሊያን አጭር ንግግር የሚያደርጉ ሲሆን በእለቱ በቫንኩቨር ነዋሪዎች ስም የምስጋናና የሽልማት ስነ ስርአትም እንደሚደረግ አዘጋጆቹ ገልጸዋል።
በቫንኩቨር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን በሌላ ሀገራት እንደሚኖሩት ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ወ/ት ብርቱካን ከታሰረችበት እለት ጀምሮ የተለያዩ ዝግጅቶችን በማድረግና በቤተሰቦቿም በሷም ላይ የሞራል ውድቀት እንዳይከሰት የገንዘብ፣ የሞራልና የሀሳብ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸው የሚታወቅ ሲሆን በተለይ ሴቶች እህቶች ያደረጉትን አስተዋጽኦም ስንዘግብ መቆየታችን ይታወሳል።



