”ሂሩት በቀለ ሞተች” የሚባለው ወሬ ሐሰት መሆኑ ተረጋገጠ
ለአዲስ ድምፅ ራዲዮ ቃለምልልስ ሰጠች
Ethiopia Zare (ሐሙስ ጥቅምት 25 ቀን 2003 ዓ.ም. November 4, 2010) ፦ ”ታዋቂና ተወዳጅዋ አርቲስት ሂሩት በቀለ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታለች” ሲል በአሜሪካን ሀገር የሚገኘው ”የሀገር ፍቅር ራዲዮ” ባለፈው ቅዳሜ ጥቅምት 20 ቀን 2003 ዓ.ም. ያሠራጨውን ዘገባ ተከትሎ ወሬው ለበርካታ ኢትዮጵያውያን ተዳርሶ ከፍተኛ ኀዘን በኢትዮጵያውን ዘንድ ተፈጥሮ ነበር። ዜናው ሐሰት መሆኑንና አርቲስቷ በሕይወት እንደምትገኝ ከአዲስ ድምፅ ራዲዮ ጋር ቃለምልልስ በማድረጓ ተረጋግጧል።
ባሁኑ ጊዜ በአሜሪካን ሀገር የምትኖረዋ ሂሩት በቀለ ከዚህ ዓለም በሞት እንዳልተለየች ያረጋገጠችው ለአዲስ ድምፅ ሬድዮ ጣቢያ በሰጠችው ቃለ ምልልስ ነው። ሂሩት ስለዚሁ ጉዳይ ስትገልጽ ወሬው በሰፊው ተሰራጭቶ ብዙ አድናቂዎቿን፣ ልጆቿና ወዳጅ ዘመዶቿን ጭምር አስደንግጦ እንደነበር ገልጻ፤ እሷ ግን በአሁኑ ሰዓት በመልካም ጤንነት ላይ እንደምትገኝ አሳውቃለች።
ሂሩት አያይዛም ስትናገር፤ ”... ይህን ሁኔታ ስሰማ ተገረምኩኝ፤ ነገር ግን ይህን ያወራብኝን ’እግዚአብሔር ይባርከው!’ ከማለት በቀር የምለው የለኝም። ሁላችሁም አትጨነቁ እግዚአብሔር እንድሞት ሳይሆን እንዳገለግለው የመረጠኝ በመሆኔ ገና አገለግለዋለሁ። በሕይወት ቆሜ ህዝብ ምን ያህል እንደሚወደኝ ማወቄ ትልቅ ደስታ ሰጥቶኛል። ሁላችሁንም አመሰግናለሁ!” ብላለች።
ሂሩት በቀለ ከ1951 ዓ.ም. ጀምሮ በጦር ሠራዊትና በፖሊስ ኦኬስትራ በድምፃዊነት ለሰላሳ ዓመት ያህል ያገለገለች ስትሆን፤ ለሃያ አንድ ዓመት ደግሞ ከሙዚቃው ዓለም ተለይታ ቆይታለች። ሂሩት በአሁኑ ጊዜ ሰባ አንድ ዓመት አዛውንት ስትሆን፤ በጥሩ ጤንነት በአሜሪካን ሀገር እንደምትኖርም እራሷ ገልጻለች።
የሀገር ፍቅር ራዲዮ ያሠራጨውን ሐሰተኛ ዜና ለማዳመጥ ከዚህ በታች ያለውን የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!
አዲስ ድምፅ ራዲዮ ከሂሩት በቀለ ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ ለማድመጥ ከዚህ በታች ያለውን የማጫወቻ ቁልፍ ይጫኑ!



