በኤርትራ ያሉ የኢትዮጵያ ታጋዮች ስጋት ላይ ናቸው

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ኅዳር 25 ቀን 2003 ዓ.ም. December 4, 2010)፦ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ሀይል ባልደረባና ከጥቂት አመታት በፊት የአርበኞች ግንባር መስራችና ምክትል ሊቀመንበር፡ የነበረው ኮሎኔል ታደሰ ሙሉነህ፡ ከኦክቶበር 25 ቀን ጀምሮ በአስመራ ከመኖሪያ ቤታቸው ታፍነው ተወስደው መታሰራቸውንና እስካሁንም የደረሱበት እንዳልታወቀ በአስመራ የሚገኙ ምንጮቻችን ገለጹ።

 

ኮሎኔል ታደሰ ከኢትዮጵያ አየር ሀይል በሕወሀት/ኢህአዴግ ከተወገዱ በኋላ በኤርትራ የሚገኝ የቀድሞ የስራ ባልደረባው ግብዣ መሰረት ቀደም ሲል የኤርትራን አየር ሀይል ያቋቋሙና ብዙ የኤርትራን አየር ሀይል አባላት ላለፉት አስራ ስምንት አመታት ያሰለጠኑ ሲሆን፡ ከጥቂት አመታት ወዲህ ግን፡ በአርበኞች ግንባር ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያትና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች በአስመራ በቁም እስር ላይ ቆይተው ነበር።

 

የኤርትራ መንግስት ኮሎኔሉን ከአካባቢው እንዳይንቀሳቀሱ አግዷቸው የከረመ ቢሆንም ባለፈው ኦክቶበር 25 ቀን ግን ከኤርትራ ደህንነት ክፍል የመጡ ታጣቂዎች ይፈለጋሉ ብለው ተወስደዋቸው እስካሁን ድረስ የደረሱበት እንዳልታወቀ ተገልጿል። ከዚህ ቀደም ኤርትራ ውስጥ የሚታገሉ ድርጅቶች አመራር አባላት እንደሚታሰሩና አንዳንዴም መድረሻቸው እንደሚጠፋ፣ እንዲሁም እንደሚገደሉ የሚነገር ሲሆን ብዙ ተከራካሪዎች “ይሄ ወያኔ ሆን ብሎ በኤርትራ በኩል የሚደረገውን ትግል ለማዳከም የሚያስወራው ወሬ” አድርገው ይቆጥሩት እንደነበር ይታወቃል። ይሁን እንጂ በኤርትራ የኢትዮጵያዊያን መለያ የሆነው የኮሎኔል ታደሰ ድንገተኛ መታሰርና መሰወር ግን ትልቅ ጥያቄ እንደሚያስነሳና የኤርትራ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ አሳማኝ ማብራሪያ ካልሰጠ በስቀር ኢትዮጵያዊያን ችላ የማይሉት ጉዳይ እንደሆነና በኤርትራ በኩል ለመታገል ቆርጠው የተነሱትን ሰዎች ጥርጣሬ ላይ እንደሚጥል አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።

 

ስማቸውን መጥቀስ ያልፈለጉና በኤርትራ በኩል መታገልን አጥብቀው የሚደግፉ አስተያየት ሰጪ፡ የኮሎኔል ታደስን መታሰር ለማመን እንደሚቸገሩና፡ እውነትም ከታሰሩ ግን፡ “በዚህ በኤርትራ በኩል የመታገልን ሀሳብ ለህዝቡ ለማሳመን ደፋ ቀና በምንልበት ሰዓት እንዲህ ያለውን ድርጊት ለማብራራት የሚያስቸግርና፡ ሰዎችን ማሳመን ፈታኝ” እንደሚሆን ተናግረዋል።

 

እኚሁ አስተያየት ሰጪ አክለውም፡ “ማንም ሰው ከሌላ አገር ሲጠጋ የአገሪቱን ህግ ሊጥስና ሊታሰር የሚችልበት ሁኔታ ቢኖርም፡ የሚታሰሩ ሰዎች ፍርድ ቤት ቀርበው መዳኘት እንዳለባቸውና ድንገት የሚሰወሩበት ሁኔታ ግን እምነትን ይቀንሳል” ብለዋል። በተለይም ”ስማቸው በክፉ የማይነሳው ኮሎኔል ታደሰ መታሰርና መሰወር ግር” እንዳላቸውና፡ “የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ ታጋዮችና ህዝብ ጋር ተስማምቶና በመተማመን መስራት ከፈለገ ባስቸኳይ ኮሎኔሉን እንዲፈታ፤ እንደ ግንቦት ሰባት ያሉ አገር ወዳድ ድርጅቶችም ነግ በኔ ብለው እንዲህ ያለውን ጉዳይ በትኩረት እንዲይዙት” አሳስበዋል። የኮሎኔል ታደሰን እስራት ጉዳይ እየተከታተልን ተጨማሪ መረጃዎችን እንዳገኘን እናቀርብላችኋለን።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ