Ethiopia Zare (እሁድ ሚያዝያ 12 ቀን 2000 ዓ.ም. April 20, 2008)፦ ባለፈው ዓመት እሁድ ጥር 13 ቀን ከንጋቱ 12 ሰዓት ከ30 ደቂቃ አካባቢ ላይ በላንጋኖ መዝናኛ ሥፍራ የተፈጸመው ፍቅረኛሞች አሳዛኝ ግድያ ተናፍሶ መቆየቱ ይታወሳል። የፍቅረኛሞቹ አሟሟት ሁኔታ አሁንም ድረስ አሳዛኝ ነው። ገዳይ ለግድያው የተጠቀመበትን ሽጉጥ የተቀበለው ከእናቱ የመሆኑ ወሬ መሰማት ደግሞ የሁሉንም ሰው ቀልብ ሲስብ፤ ለሟች ቤተሰቦች መሪር ኀዘንን መፍጠሩ ተዘገበ።

 

በላንጋኖ የተገደሉት ሟች የማነ መስፍን እና ሟች የትናየት ጌቱ የተባሉት ሁለቱ ፍቅረኛሞችን በቡድን ሆነው ገድለዋል በተባሉ ቤተሰቦች ላይ ቀርቦ የነበረውን ክስ የፍርድ ሂደት ተጠናቋል። ገዳይ በ18 ዓመት ጽኑ እስራት፣ መሣሪያ ያቀበሉ እናት በ15 ዓመት ጽኑ እስራት፣ ያለ ጥንቃቄ መሣሪያ ያስቀመጡ አባት ደግሞ በሁለት ወር እስራት እንዲቀጡ ሲወሰን፤ ተባባሪ ነው ተብሎ የተከሰሰ ወንድም በነፃ ተሰናብቷል። ውሳኔው የሟች ቤተሰቦችን አስቆጥቷል፤ አሳዝኗል።

 

የሟች የትናየት ጌቱ አባት አቶ ጌቱ ደበበ ይባላሉ። በልጃቸው ሞት እጅግ ማዘናቸውን ገልጸው፤ ስለፍርዱ ሁኔታ አስተያየት ሲሰጡ በሟቾች ላይ አደጋውን ካደረሱት ግለሰቦች ጋር እንደማይተዋወቁ፣ ለሁለት ዓመታት ያህል የልጃቸው እጮኛ መሆኑን የሚያውቁት ሟች የማነ መስፍንን እንደሆነ ተናግረዋል።

 

"ገዳይ" ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ እንቅልፍ የጣላቸውን ሁለት ሰዎች ሆን ብሎ አስቦና አቅዶ በግፍ ገድሎአቸው እያለ የተሰጠው የቅጣት ውሳኔ በቂ አይደለም ይላሉ።

 

ልጃቸውንና የልጃቸውን እጮኛ አባሪ ተባባሪ ሆነው አገር አቋርጠው ሄደው እናት መሳሪያ አቀባይ፣ ልጅ ተኩሶ ገዳይ ወንድም መስኮት ሰብሮ በመግባት ተባባሪ ሆነው ግድያ በፈፀሙ ሰዎች ላይ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ መሆናቸውን ካረጋገጠ በኋላ የሰጠው ቅጣት ግን ፍትሃዊ ያልሆነ ነው ይላሉ።

 

አቶ ተስፋዬ መስፍን፣ የሟች የማነ መስፍን ታላቅ ወንድም ናቸው። አስበውና አቅደው በቡድን ሆነው ሁለት ግለሰቦችን ጨፍጭፈው በግፍ በገድሉ ግለሰቦች ላይ የተሰጠው የቅጣት ውሳኔ ሕጉን ያልተከተለና ፍትሃዊ ያልሆነ በመሆኑ ዓቃቤ ሕግ ይግባኝ እንዲጠይቅላቸው ማመልከታቸውን ተናግረዋል።

 

የሁለቱ ሟች ፍቅረኛሞች ቤተሰቦች፣ በቅጣት ውሳኔው "የሞት ፍርድ" ባይሰጥ እንኳን የዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ጠብቀው እንደነበር ገልጸዋል።

 

ፍርድ ቤቱ በተከሳሾቹ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሲሰጥ እንዳረጋገጠው፤ ሟች አቶ የማነ መስፍን እና የትናየት ጌቱ ጥር 12 ቀን 1999 ዓ.ም. ምሽት ላይ ላንጋኖ በቀለ ሞላ ሆቴል ደርሰዋል። ሲዝናኑ አምሽተው አመሻሹ ላይ ወደ ክፍላቸው ገብተው መተኛታቸው ታውቋል።

 

እሁድ ጥር 13 ቀን ከንጋቱ 12 ሰዓት ከ30 ደቂቃ አካባቢ "ገዳይ" መሆኑ በፍርድ ቤት የተረጋገጠበት የእዮሲያስ አበራ እናት ወ/ሮ ትርንጐ ወ/ሚካኤል፤ ለዓለም አበራ እና አብያለው አበራ የተባሉ ሁለት ወንድሞቹንና መላኩ ግዛው የተባለ ጓደኛውን ይዘው ላንጋኖ ይደርሳሉ።

 

እናት ወ/ሮ ትርንጐ በባለቤታቸው ስም ፈቃድ ያለውን ሽጉጥ ይዘው በመምጣት ለልጃቸው ያቀብላሉ፣ ልጅ መስኮት ሰብሮ በመግባት ፍቅረኛሞቹ በተኙበት በጥይት ደብድቦ መግደሉ በፍርድ ቤት ተረጋግጧል።

 

የሕክምና ማስረጃው እንዳረጋገጠውም ሟች የማነ መስፍን በአራት ጥይት ጭንቅላቱ እና ደረቱ ላይ መመታቱን፣ ሟች የትናየት ጌቱ ደግሞ በልብዋ አካባቢ በሁለት ጥይት መመታቷ ታውቋል።

 

በወቅቱ ወንጀሉን ፈፅመዋል በሚል ተጠርጥረው የተያዙት እናት ወ/ሮ ትርንጎ ወ/ሚካኤል፣ እዮስያስ አበራ፣ አብያለው አበራ፣ ለዓለም አበራ እና መላኩ ግዛው ወደ ምስራቅ ሸዋ አርሲ ነገሌ ፖለስ ጣቢያ ተወስደው ታስረዋል።

 

የምስራቅ ሸዋ አርሲ ነገሌ ፖሊስ ክሱን መስርቶ በምስራቅ ሸዋ አርሲ ነገሌ ዞን ፍርድ ቤት ጉዳዩ መታየት ከጀመረ በኋላ ፍርድ ቤቱ ወደ ሻሸመኔ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዲዘዋወር በመወሰኑ በወንጀሉ የተጠረጠሩት ግለሰቦች ወደ ሻሸመኔ ወህኒ ቤት እንዲዛወሩ ተደርጓል።

 

ጉዳዩ ከሻሸመኔ ወደ አዳማ ፍርድ ቤት በመምጣት ሚያዝያ 1 ቀን 2000 ዓ.ም. ውሳኔ አግኝቷል። በውሳኔው ገዳይ እዮስያስ አበራ 18 ዓመት፣ እናት ወ/ሮ ትርንጐ ወ/ሚካኤል 15 ዓመት ሲፈርድባቸው፣ አባት ሁለት ወር፣ ወንድም ደግሞ በነፃ ተለቀዋል። የሟቾቹ ቤተሰቦች እንደሚሉት ሟች አቶ የማነ መስፍንና ሟች ወይዘሪት የትናየት ጌቱ ቤተሰብ የሚያውቅላቸው የሦስት ዓመት ፍቅረኛሞች ናቸው ብለዋል።

የሟቾቹ ቤተሰቦች ግን ልጆቻችን፣ ወንድማችንና እህታችንን በግፍ ለገደሉብን የተሰጠው ፍርድ ፍትሃዊ ያልሆነና ሕግን የሚፃረር ነው፤ ትክክለኛ ውሳኔያችንን በይግባኝ እጠይቃለን በማለት ተቃውሞአቸውን አቅርበዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ