አንጋፋው የእግር ኳስ ሰው መንግሥቱ ወርቁ በ70 አመቱ አረፈ
በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ ግምባር ቀደም ተጠቃሽ የሆነውና ከቅዱስ ጊዮርጊስ ተጨዋችነት እስከ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣንነት ስኬታማ ታሪኮችን ያስመዘገበው ታላቁ የእግር ኳስ ሰው መንግሥቱ ወርቁ ከዚህ አለም በሞት መለየቱ ታወቀ።
ኮከቡ ተጫዋች መንግሥቱ ወርቁ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በተለያዩ ሀገራት ባደረጋቸው ግጥሚያዎች አኩሪ ድሎችን ያቀዳጀ መሆኑ የሚታወቅ ከመሆኑም በላይ የብሄራዊ ቡድኑን በማሰልጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉ ይታወቃል።
መንግሥቱ ወርቁ የግብጹን አል ዛማሊክ ክለብን ጨምሮ በተለያዩ የኢጣሊያና ፈረንሳይ ክለቦች እንዲጫወት ተጠይቆ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን ስምንት ቁጥርንና የ ‘V‘ ምልክት ያለውን ቅዱስ ጊወርጊስ ቡድንን ጥሎ መውጣት እንደክህደት በመቁጠር እድሜውን ለቅዱስ ጊወርጊስ አሳልፎ መስጠቱን ብዙ አድናቂዎቹ ያስታውሳሉ።
አንጋፋው የእግርኳስ ንጉስ መንግሥቱ ወርቁ 3ኛውን የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ግብጽን ሶስት ለምንም ባሸነፈችበት ወቅት ሁለት ድንቅ ጎሎችን በማስቆጠር ኮከብ ጎል አግቢ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን ከ1958 እስከ 1972 ድረስ በአለም አቀፍ ተጨዋችነት ሀገሩን አገልግሏል።
መንግሥቱ የ7ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ ከምድቧ የመጨረሻ በመሆኗ እጅግ አዝኖና ተስፋ ቆርጦ ጡረታ ለመውጣቱ ምክንያት እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫ ታሪክ 10 ጎሎችን በማስቆጠር የ7ኛ ደረጃን እስካሁን ድረስ መያዙ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ለአንጋፋው የእግር ኳስ ሰው ቤተሰቦችና አድናቂዎቹ መጽናናትን ታገኙ ዘንድ እንመኛለን።



