“የኳታር መንግሥት ትዕቢተኛ ነው” - ኢህአዴግ
- ኢህአዴግ ከኳታር ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን አቋረጠ
- አል-ጀዚራ ከምክንያቶቹ አንዱ ነው
- ሦስቱን የአል-ጀዚራ ሪፖርቶች ይዘናል
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሚያዝያ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. April 22, 2008)፦ “ኳታር የኢትዮጵያን ብሔራዊ ደህንነት ለመጉዳት ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም። በኢትዮጵያ አለመረጋጋትን ለመፍጠርና ፀጥታዋን ለማናጋት የተነሱ ኃይሎች ሁሉ የኳታር ድጋፍና አይዞህ ባይነት አልተለያቸውም” በሚል የኢህአዴግ መንግሥት ከኳታር ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማቋረጡ ታወቀ።
ኢህአዴግ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካኝነት በትናንት ዕለት ግንኙነቱን ያቋረጠበትን ምክንያት ሲያብራራ፤ ጉዳዩ ኳታር ከኤርትራ ጋር ካላት ጠንካራ ግንኙት የዘለለ መሆኑንና፤ በሶማሊያና በሌሎች አካባቢዎች ለሚንቀሳቀሱ አሸባሪዎች በቀጥታና በተዘዋዋሪ ድጋፏን እንደምትሰጥና የመገናኛ ብዙኃንንም መጠቀሟን ገልጿል።
አክሎም “… ኳታር ለታጣቂ ተቃዋሚዎችና በጎረቤት ላሉ አዝማቾቻቸው የድጋፍ ምንጭ መሆኗ የሚታወቅ ነው። በአጠቃላይ በሶማሊያም ይሁን በሌሎች የአፍሪካ ቀንድ አካባቢዎች በኢትዮጵያም ውስጥ ጭምር ከዋነኞቹ የአሸባሪነትና የጽንፈኝነት ደጋፊዎች መካከል አንዷ ናት። …” ሲል ኳታርን ወንጅሏል።
የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከኳታር መንግሥት ጋር በጉዳዩ ላይ ደጋግሞ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ማድረጉንና አለመሳካቱን አክሎ ገልጿል። በኢህአዴግ የሚመራው መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለዚህ ውንጀላው በቂና የማያሻሙ ማስረጃዎች እንዳሉትና ኳታር ከድርጊቷ አለመታቀቧንና አሻፈረኝ ብላለች ብሏል።
“… ምናልባትም ለተደረጉት ጥረቶች ሁሉ በጎ ምላሽ ያለመስጠቷ ምክንያት ምንጭ ግልጽ የሆነው ትዕቢት ነው” ሲል መስሪያ ቤቱ ገልጾ፤ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱን ለማቋረጥ መገደዱን አስታውቋል።
ኢትዮጵያ ዛሬ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የጠቃቸው የፖለቲካ ታዛቢዎች አል-ጀዚራ የተሰኘው የቴሌቭዥን ጣቢያ በቅርቡ ያስተላለፈው ሪፖርት ጉዳዩን እንዳባባሰው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
ቴሌቭዥን ጣቢያው የኳታር መንግሥት የማይወዳቸው ሀገራት መንግሥታት ላይ ፕሮፓጋንዳ ይነዛል የሚሉት እንዳሉ ሁሉ፤ የሚያሞካሹትና የሚያወድሱትም በርካቶች መሆናቸው ይነገራል። የቴሌቭዥን ጣቢያው በዓለም በርካታ ጋዜጠኞች ካሏቸውና ትላልቅ ጣቢያዎች አንዱ ነው።
አል-ጀዚራ ቲቪ ዋና መስሪያ ቤቱ ዶሃ፣ ኳታር ሲሆን ባለቤቱ ሼህ ሐማድ ቢን ተኻመር አል-ተኻኒ ናቸው። የኳታሩ ኤሚር ሼህ ሐማድ ቢን ኻሊፋ 150 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሰጥተውት በ1996 እ.ኤ.አ. ነው የተቋቋመው።
በተለይ የአል-ጀዚራ እንግሊዝኛ ጣቢያ ኦብነግን (የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃ አውጪ ግንባርን) በተመለከተ ካስተላለፋቸው ሪፖርቶች ውስጥ ሦስቱን ከዚህ በታች ያሉት ናቸው።
ክፍል አንድ
ክፍል ሁለት
ክፍል ሦስት



