ኢትዮጵያ የኤርትራ ሸብርተኞችን ያዝኩ አለች
Ethiopia Zare (ሰኞ ጥር 16 ቀን 2003 ዓ.ም. January 24, 2011)፦ የአፋር ክልልን አቋርጠው በመግባት በኢትዮጵያ ውስጥ የሽብር ጥቃት ሊያደርሱ ከሻእቢያ የተላኩ ስልጡን ሽብርተኞች መያዛቸው ተገለጸ።
ቁጥራቸው ሰባት የሚደርሱትና በቁጥጥር ስር መሆናቸው የተገለጹት ሚሊሻዎችን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን በማሳየትና የአንዱን የምስክርነት ቃል በማሰማት የተስተዋለው ይሄው ዘገባ ልዩ ልዩ የጦር መሳሪያዎችን ያካተተና ለፈንጅ ስራ የሚውሉ ቁሳቁሶች መያዛቸውን አትቷል።
ሚሊሻዎቹ በተለያዩ ተቋማትና ብዙ ህዝብ ይገኙባቸዋል በተባሉ ቦታዎች የሽብር ስራ ለመስራትና ለማምለጥ የሚችሉባቸውን በቂ ስልጠናዎችን የወሰዱ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን በተለይ በነዳጅ ማደያዎች፣ የህዝብ ማመላለሻ መኪናዎችና የገበያ ቦታዎች ለጥቃቱ ዋና ኢላማዎች እንደነበሩ ተገልጿል።
ይህንን ከኢትዮጵያው አገዛዝ የወጣ መረጃ ዋቢ በማድረግ ነዋሪነታቸውን በአሜሪካን ሀገር ያደረጉ የፖለቲካ ተንታኝ ሰፊ ትንተና የሰጡበት ከመሆኑም በላይ በአሁኑ ሰአት የኢህአዴግ አገዛዝ የተለያዩ ፖለቲካዊ ጨዋታወችን በተለያዩ ዘርፎች በመጫወት ላይ መሆኑን ጠቅሰው ከአሁን በፊት ተመሳሳይ የውሸት ማስረጃዎችንና ምስክሮችን በመንግስት መገናኛዎች በማሳየትና በማሰማት ለተራ የፖለቲካ ትርፍ ሲባል ብቻ በመዋላቸውና የመንግስት መገናኛ ብዙሀኖች በህዝብ ዘንድ እምነት በማጣታቸው ይህ አሁን የተባለው የጥቃት ሙከራ እውነት ቢሆን እንኳን ህዝቡ አምኖ እንዲቀበልና እንዲዘጋጅ ከማድረጉ አኳያ አሉታዊ ችግር እንደሚያስከትል አብራርተዋል።
የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ከተከሰተ 1998 ወዲህ ሁለቱም በተለያዩ ተመሳሳይ ውንጀላዎች ሲካሰሱ መቆየታቸው ይታወቃል።



