የቴሌ ኮሙኒኬሽን ሰራተኞች ሮሮ መልስ አላገኘም
ስምንት ሺህ የሚደርሱ ሰራተኞች ተባረዋል
Ethiopia Zare (ረቡዕ የካቲት 23 ቀን 2003 ዓ.ም. March 2, 2011)፦ የኢትዮጵያ ቴሌ ኮሞኒኬሽን አስተዳደር ፈርሶ በፈረንሳዩ ፍራንስ ቴልኮም ቁጥጥር ስር እንዲገባ ከተደረገ ጀምሮ ስምንት ሺህ የሚደርሱ የቴሌ ሰራተኞች ከተባረሩ በኋላ የሚያሰሙት ሮሮ ተቀባይነት እንዳላገኘ ምንጮች ገለጹ።
በተደጋጋሚ ስብሰባ ሲጠሩ የሰነበቱት ሰራተኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ ምንም አይነት ምላሽ እንደማያገኙና ሌላ አማራጮችን እንዲጠቀሙ በግልጽ እየተነገራቸው መሆኑን ለመረዳት ችለናል። በአትራፊነቱ የሚታወቀው ቴሌ ኮሞኒኬሽን ሰራተኞች ጋር በተደረጉ ስብሰባዎች በምን ምክንያት ለፈረንሳዩ ካምፓኒ ሊሰጥ እንደቻለ ምንም አይነት ማብራሪያ እንዳልተሰጠበት ታውቋል።
ጉዳዩን እንዲከታተሉና መፍትሄ እንዲያፈላልጉ የተሰየሙት የቀድሞው የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ አርካበ እቁባይ መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ለሰራተኞቹ የስራ መመለስ ተስፋ እንደሌለ በግልጽ ማስቀመጣቸው ተገልጿል።
ፍራንስ ቴሌኮም አዲስ በሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ቴሌ ኮሚኒኬሽን አዳዲስ የውጭ ሀገር ሰራተኞችን ቀጥሯል። በአሁኑ ሰአት ቤተሰቦቻቸው በከፍተኛ ስጋትና ችግር ላይ የሚገኑት ሰራተኞች መንግስት አትራፊ የሆነውን ድርጅ በዚህ አይነት መልኩ ለውጭ ሀገር ዜጎች አሳልፎ መስጠቱ እጅግ ስህተት ነው ሲሉ አስምረውበታል።



