የትራንስፖርት እና የነዳጅ ዋጋ እያሻቀበ ነው

Ethiopia Zare (አርብ መጋቢት 2 ቀን 2003 ዓ.ም. March 11, 2011)፦ የዋጋ ማስተካከያ የተደረገባቸው ሸቀጣ ሸቀጦች በአብዛኞቹ ከገበያ መጥፋታቸውና በተለይ ስኳርና ዘይት በገበያ ላይ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ሸማቾች ገለጹ። በመጓጓዣ ዋጋ ላይ እስከ 1 ብር ከ95 ሣ. ጭማሪ ተደርጓል።

 

በአዲስ አበባና በአንዳንድ የክፍለሀገር ከተሞች ያለውን የገበያ ሁኔታ ለማጣራት ባደረግነው ጥረት መሰረት ስኳርና ዘይት ለማግኘት የተወሳሰበ አሰራር እንደተፈጠረባቸው በምሬት የገለጹት ነጋዴዎች ‘ምንም አይነት አቅርቦት በሌለበት ሁኔታ የተደረገ የዋጋ ማሻሻያ ከሸማቾች ጋር ብቻ ሳይሆን ከታላላቅ አቅራቢ ኩባንያዎች እና ከመንግስት ጋር እያጋጨን ነው’ ሲሉ በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጸዋል።

 

ሸማቾች እንደሚሉት ደግሞ ስኳር ከችርቻሮ ውጭ በኪሎና ከዚያ በላይ ለመግዛት ከታላላቅ አከፋፋይ ኩባንያዎች ካልሆነም ከገዥው ፓርቲ ባለስልጣናት ጋር ቅርብ ትስስር ለሌለው ነጻ የሀገሪቱ ዜጋ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን የገለጹ ሲሆን በዚሁ ባልተጠና የገበያ ማስተካከያ ምክንያት ኑሯቸው ከድጡ ወደ ማጡ ለመሆን እንደተገደደ ገልጸዋል።

 

በአብዛኛው የገጠር ነዋሪ ዘንድ ዘይትና ስኳር ለማግኘት የማይሞከር ከመሆኑም በላይ በከተማዎች አካባቢ ሸቀጦቹን ለማግኘት ወረፋው የማይነካ እየሆነ መምጣቱን የገለጹት ሸማቾች በቀላሉ ልጆቻቸውን ሻይ አጠጥቶ ወደ ትምህርት ቤት መላክ አለመቻላቸውንና ያለ ዘይት የተሰራ ምግብ በማቅረብ ላይ መሆናቸውን በምሬት ገልጸዋል።

 

መንግስት ሸቀጦቹን ከውጭ ሀገራት በብዛት ሊያስመጣ መሆኑን በቁጥጥሩ ስር በሚገኙ የመገናኛ ብዙሀን እየገለጸ ሲሆን አገዛዙ አሁንም ተጨማሪ ጥናት ያልተደረገበት ግብታዊ ስራ በመስራት ላይ መሆኑንና ከውጭ ሀገር ምርቶችን ማስመጣት እስከመቼ ሊያዛልቀው እንደሚችል ግንዛቤ ውስጥ መግባት አለበት። ሲሉ በኢኮኖሚ የሙያ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ትችት ሰንዝረዋል።

 

በተጨማሪም የጋዝ ዋጋ ከእለት ወደ እለት እየጨመረ መሆኑን የገለጹ እማኞች በየወሩ በሚደረገው በዚሁ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በወጣ የትራንስፖርት ታሪፍ ጭማሪ መሰረት በእያንዳንዱ የታክሲና የማመላለሻ አገልግሎቶች ላይ ከ15ሣንቲም እስከ 1ብር ከ95ሣንቲም የሚደርስ የታሪፍ ጭማሪ የተደረገ ሲሆን 2ብር ከ65ሣ. የነበረው የአንድ ፌርማታ ዋጋ 2 ብር ከ85 ሣ፣ 3 ብር ከ20 ሣ. የነበረው 3 ብር ከ45 ሣ፣ 6 ብር ከ50 ሣ. የተከፈለበት አሁን 7 ብር ከ25 ሣ. ከማሻቀቡም በላይ በከተማ አውቶቡሶች ላይ ከ1 ብር ከ30 ሣ እስከ 1 ብር ከ95 ሣ. የሚደርስ የታሪፍ ጭማሪ መደረጉን ለማወቅ ችለናል። ጭማሪው የረጅም ርቀት ተጓዥ አውቶቡሶችን ያካተተ ሲሆን በየ100 ኪ.ሜትር ርቀት ጭምሪው ከፍ እንደሚል ለማወቅ ችለናል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ