ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ ሊሰጥ ነው
Ethiopia Zare ( ቅዳሜ መጋቢት 3 ቀን 2003 ዓ.ም. March 12, 2011)፦ ሚኒሊክ፣ አስኳልና ሳተናው በተባሉት ጋዜጦቹ የሚታወቀውና በአሁኑ ሰዓት በህትመት ስራ ላይ እንዳይሳተፍ የታገደው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፤ በተለይ ለአቶ መለስ ዜናዊ በጻፈው ግልጽ ደብዳቤና በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ዙሪያ በሬዲዮ ውይይት እንደሚያደርግ ተገለጸ።
ከካናዳዋ መናገሻ ኦታዋ በየሳምንቱ ከሚተላለፈው የአማርኛ ስርጭት አዘጋጆች ጋር በቀጥታ ውይይት የሚያደርገው ጋዜጠኛ እስክንድር በአረብና ሰሜን አፍሪካ ሀገራት የሚካሄደው ህዝባዊ አመጽ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ አንድምታ ጋር በማያያዝ ያለውን ልምድ የሚያካፍል ከመሆኑም በላይ ከአድማጮች የሚቀርቡ ጥያቄዎችንም እንደሚያስተናግድ ታውቋል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ከሁለት ሳምንት በፊት ለአቶ መለስ ዜናዊ ህዝቡ ለውጥና ከስልጣን እንዲወርዱ እንደሚፈልግ በላከው ግልጽ ደብዳቤ http://ethiomedia.com/above/2220.html ራሱ ለረጅም ግዜ ከኖረባትና ከተማረባት አሜሪካ ተሞክሮ ጋር በማጣቀስ ኢትዮጵያ ውስጥ ለምን ለውጥ እንደሚያስለፈልግ አትቷል። “እንዳለመታደል ሆኖ ከአሜሪካ መሪዎች በተቃራኒ የኢትዮጵያ መሪዎች ከረዳቶቻቸው እውነተኛ ምክር አያገኙም። በኢትዮጵያ በዚህ አርባ አመት ውስጥ ብዙ ነገሮች እንደተለዋወጡ፡ አንዳንድ ነገሮች ግን ፈጽሞ እዚያው ባሉበት እንዳሉ ያስረዳው እስክንደር ከነዚህም አንዱ መሪዎች ማወቅ የሚገባቸውን ሳይሆን መስማት የሚፈልጉትን ብቻ ነው አንደሚነገራቸው አስረድቷል።
ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ለአቶ መለስ በጻፈው ግልፅ ደብዳቤ ላይ በመቀጠልም ልክ በኮሎኔል መንግስቱ ግዜ እንደነበረው፡ “በዚህ የስልጣን ዘመንዎት ስልጣንና ጥቅም አናታቸው ውስጥ የነገሰው ረዳቶችዎ ስለኢትዮጵያ ህዝብ የሚነግሩዎት ምክር ‘በፈጣን የምጣኔ ሀብት እድገትና በተረጋጋ ፖለቲካ የፈነደቀ ህዝብ፣ ደስተኛና ተስፋ የሞላበት ወጣት እንዲሁም ያለፈለት ገበሬ፤ በሌላ አነጋገርም በመለስ የማይተካ አመራር ስር ሆኖ ወደ እድገት ሊመነጠቅ ያኮበኮበ ህዝብ” እንደሆነ፡ ነገር ግን እውነታው ያ ሳይሆን፡ ተራው የኢትዮጵያ ህዝብ “ሰማይ በነካ የዋጋ ግሽበት የተቃጠለ፡ ታይቶ በማይታወቅ ሙስና እና ለከት ያጣ ስራ እጥነት፤ በፖለቲካ ጭቆና፣ በመራር የመሬት እጥረት ያረረና የተመዘበረ ሕዝብ ነው። በጥቅሉ ሕዝቡ ለውጥ ይፈልጋል።” ሲል ጽፏል።
ቀጥሎም፡ አቶ መለስን “ለውጥ ሊያመጡ ይችሉበት የነበረውን ሀያ አመት እምሽክ አድርገው አባከኑት። እነሆ በርስዎ አመራር ‘በተግባራዊነት ቦታ ግትርነት ተንሰራፋ። በግልጽነት ቦታ ምስጢራዊነት ስር ሰደደ። በዴሞክራሲ ፈንታ ጭቆና ጣሪያ ነካ። ከችሎታ ይልቅ ዝምድናና አድርባይነት በልጠዋል፡” ብሎ በመጨረሻም፡ “አቶ መለስ የኢትዮጵያ ህዝብ በሊቢያና በሰሜን አሜሪካ እንዲሁም በአረቡ ዓለም እየሆነ ባለው ነገር እጅግ በጣም ተስፋው ለምልሟል። በልበ ሙሉነት ተሞልቷል።” ህዝቡ፤ ነገሮች ፈር ለቀው ሳይሄዱ በፊት (ደም ሳይፋሰስ ማለቱ ነው) ስልጣን እንዲለቁ ይፈልጋል።” በማለት ለአቶ መለስ ዜናዊ የጻፈውን ግልጽ ደብዳቤ ደምድሟል። በደብዳቤው ዙሪያና በኢትዮጵያ መጻኢ እድል ላይ ለመምከር፡ በኦታዋ የኢትዮጵያ ራዲዮ አዘጋጅ፡ ተክለሚካኤል አበበ ጋር ግልጽ ውይይት እንደሚያደርግ ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያስረዳል።
እስክንድር ነጋ ከሰባት ጊዜ በላይ በእስር ቤት የተጣለና በአሰቃቂ ሁኔታ የተደበደበ ሲሆን፡ ባለቤቱ የሰርካለም አሳታሚ ባለቤት ወ/ሮ ሰርካለም ፋሲልም፤ በግፍ ከነበረችበት የቃሊቲ እስር ቤት ውስጥ መውለዷ የሚታወስ ነው። እስክንድር ነጋ፡ ሕገ-መንግስታዊውን ስርአት በሀይል ለመናድ ተወንጅሎ ከታሰረበት እስርቤት ከተፈታ በኋላ፤ በግሉም በጋዜጣ አሳታሚ ድርጅቱ በኩልም ከ150 ሺህ ብር በላይ ቅጣት እንዲከፍል እንደተወሰነበት የሚታወቅ ሲሆን፤ ላለፉት ሁለት አመታት በሚጽፋቸው ጠንካራ ሳምንታዊ ፖለቲካዊ ጽሁፎች ይታወቃል። እስክንድር ነጋ ከወር በፊት አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሰዓታት ታስሮ የተለቀቀ ሲሆን፡ አሁንም በኢትዮጵያ የቱኒሲያና የግብጽ አይነት አመጽ ለመቀስቀስ ትጥራለህ በሚል ሰበብ ሊታሰር ይችላል የሚል ስጋት ይንሸራሸራል።
በዚሁ በመጭው እሁድ ማርች 13/11 ከሰዓት በኋላ በምስራቅ አሜሪካን ሰዓት አቆጣጠር ከ2-እስከ 3 ሰዓት (Sunday March 13, 2pm – 3pm) ዝግጅቱን በሚከተለው ድረ ገጽ መከታተል ይችላሉ። http://www.chuo.fm/en/home, CHUO FM 89.1, Ottawa



