ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አመጽ ሊያስነሱ እንደሚችሉ ተነበየ
በእረፍት ላይ የሰነበቱት ተማሪዎች ወደግቢ እየተመለሱ ነው
ጠንካራ ፖለቲካዊ ጽሁፎችን በመጻፍና ድፍረት የተሞላባቸውን ሀሳቦች በማስተጋባት የሚታወቀው፡ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፡ ከእረፍት እየተመለሱ ያሉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንደ ግብጽና ቱኒዚያ አጋሮቻቸው የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ሁኔታ ሊቀይር የሚችል አመጽ ሊያስነሱ እንደሚችሉ ተነበየ።
እስክንድር ነጋ በያዝነው ሳምንት አርብ እለት “Ethiopia: Protest and Addis Ababa University” በሚል ርዕስ ባወጣው ጽሁፍ ላይ፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ባሳለፈው ስልሳ አመት እድሜው፤ በተፈራረቁበት ሶስቱ መንግስታት አስተዳደር ውስጥ የህብረተሰቡን ብሶት ይዞ በመነሳትና ለለውጥ በመታገል የነበራቸውን ሚና አብራርቶ፡ በዚህ በያዝነው የፈረንጆች አመት መጀመሪያ ጀምሮ በግብጽና በተቀሩት የአረብ አገራት እንደታየው፡ በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ጥያቄ ሊያስነሱ ይችላሉ የሚል ጠንካራ እምነት እንዳለውና ምልክቶችም እየታዩ እንደሆነ ተናግሯል።
እስክንድር በዚህ ጽሁፉ፡ በአፍሪካ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ዘግይቶ የተጀመረው የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ በ1950ዎቹ በአጼ ሀይለስላሴ ላይ የተደረገውን (የነመንግስቱ ንዋይን) መፈንቅለ መንግስት ደግፈው ሲወጡ ተጀምሮ፡ በምእራቡ ዓለም በተደረገው የተማሪዎች ፀረ-ቬትናም ጦርነት እንቅስቀሰሴ ተጠናክሮ ቀጥሎ፤ በ1970ዎቹ ድረስ በቀይ ሽብር እስኪጨናገፍ ድረስ እንደዘለቀ ጠቅሶ፡ ለቀጣዮቹ አስር አመታት ከተዳከመ በኋላ፡ በ1981 የተደረገውን መፈንቅለ መንግስት ተከትሎ 13 ጄነራሎች ሲረሸኑ፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ትንሽ እንቅስቃሴ እንደገና እንዳንሰራራ ጽፏል። ሆኖም የመገንጠል መብትን መሰረት ያደረገ ጽኑ ክፍፍል በተማሪዎቹ ውስጥ ከመስፈኑ የተነሳ፡ደርግን የሚያሰጋው የተማሪዎች አንድነት ሳይመሰረት ቆይቶ፡ የደርግ መንስስት ወድቆ የሕወሀት/ኢህአዴግ አገዛዝ ከተተካ በኋላ፡ ከ1991 ዓ.ም. ጀምሮ ነጻ ፕሬስና የተሻለ የመደራጀት መብት ከመጣ በኋላም፡ ተማሪዎች በሀይለ ስላሴ ግዜ የነበራቸውን በነጻ የመደራጀትና ሀሳብን የማንሸራሸር መብታቸውን ሳኢጠቀሙበት እንደቆዩ ገልጿል።
ይሁን እንጂ፡ እስክንድር እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1993 ዓ.ም. የተባበሩት መንግስታት ዋና ጸሀፊ ቡትሮስ ቡትሮስ ጋሊን ጉብኝትና የኤርትራን መገንጠል ተቃውሞ የተደረገውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አመጽ ዘሎት፡ ሌላ አስር አመት ካለፈ በኋላ፡ በ2001 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፤ ዩኒቨርስቲው የትምህር ነጻነትንና ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፡ እንዲሁም የመቻቻልን ፖሊሲ እንዲያራምድ ባንድነት በመቆም በአመጽ ተነሱ። በዚያም አመጽ ምክንያት ብዙ ተማሪዎችን ደግፈው የወጡ ወጣቶች ህይወት ተቀጥፎ ሕወሀት አመጹን አከሸፈው ሲል አትቷል።
ከ1960ዎቹ እስከ 1970ዎቹ፡ ከ1970ዎቹ እስከ 1980ዎቹ፡ ከ1980ዎቹ እስከ 1990ዎቹ የነበረው በየአስር አመታት ልዩነት የሚነሳ የተማሪዎች የመብት ጥያቄ አመጽ መሰረት አድርጎ እንዲሁም አሁን ባለው አመጽ ቀስቀሳሽ ውጫዊና ውስጣዊ ምክንያቶች የተነሳ፡ ዘንድሮም የዚህ የየአስር አመት ልማድ ሊደገምና የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች አመጽ ሊያስነሱ ይችላሉ የሚል ትንቢት ተናግሯል።
ከአምስት ሳምንታት በፊት በሚጽፋቸው ድፍረትና ብስለት የተመላባቸው አብዮታዊ ጽሁፎቹ ምክንያት የተነሳ ለሰኣታት ታስሮ የነበረው እስክንድር ነጋ፡ ሙባረክ ሲወርድ፡ ጋዳፊም ሲዋረድ ረፍት ላይ የነበሩት ተማሪዎች ወደትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ በመሆናቸውና የተዘጋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም መልሶ በመከፈቱ ምክንያት፡ የአዲስ አበባ ተማሪዎች ሊያምጹ ይችላሉ የሚለውን ትንቢት ተጫባጭ ሊያደርገው የሚችለውን ምክንያት እንዲህ ሲል ገልጿል፤
“እርገጠኛ የሆንበት ነገር ቢኖር፡ በግቢም ከግቢም ውጪ ባለው የነጻነት እጦት ተማሪዎች ከፍተኛ ምሬትና ጥላቻ እንዳላቸው ነው። ለብዙ ተማሪዎች፡ የኢህአዴግ 99.6 ከመቶ የምርጫ ድል ምንያህል ከህዝቡ እንደተገለለና እንደራቀ የሚያሳይ ነው። ከአመታዊ ጠቅላላ አገራዊ ምርት ይለቅ እያሻቀበ ያለው የኑሮ ውድነት፡ የተመናመነ የስራ እድል ነው የተማሪዎቹን ሀሳብ ተቆጣጥሮታል። ከቁጥጥር ውጪ የሆነው ሙስናም የዩኒቨርስቲውን ድባብ ወሮታል።”
ስለዚህም በመጪዎቹ ጥቂት ሳምንታት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በርግተኝነት ያምጻሉ ሲል ተንብዮዋል።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ታሪዎች ሊያምጹ ይችላሉ የሚለውን የእስክንድር ነጋን ትንቢት የሚያጠናክሩ ማስረጃዎችን እንደተመለከቱ ሌሎች ምንጮቻችን ገልጸዋል። በሺህዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች በድረ-ገጽና በምይል እያንሸራሸሩና የ“በቃ” ንቅናቄ መፈክሮችና ሀሳቦች እየተንሸራሸሩ እንደሆነ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ወጣት ተማሪዎች በስልክ አናግረናል።



