ሁለተኛ ካናዳዊ በኢትዮጵያ እስር ቤት ገባ

Ethiopia Zare (ረቡዕ ሚያዝያ 12 ቀን 2003 ዓ.ም April 20, 2011)፦ የ26 አመቱ ወጣት ካናዳዊ ፍዋዝ ሀርጋያ በኢትዮጵያ እስር ቤት ከሁለት ሳምንት በላይ መቆየት የካናዳ መንግስትንና ቤተሰቦቹን እንዳሳሰበ ተገለጸ።

 

የ26 ዓመቱ ወጣት ፍዋዝ በ5 አመቱ ከቤተሰቦቹ ጋር በስደት ከሀገሩ ከወጣና ካናዳ መኖሪያውን ካደረገ በኋላ የትውልድ ሀገሩን ለመጎብኘት እንደተመለሰ ለእስር እንደተዳረገ በካናዳ ዊኒፔግ ክፍለ ግዛት ነዋሪ የሆነችው እህቱ ኢፍቱ የገለጸች ሲሆን በማንኛውም የቤተሰብ አባል እንዳይጎበኝ መከልከሉን ይፋ አድርጋለች።

 

ወጣቱ ለእስር የበቃው ከካናዳ ይዟቸው የገባውን የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች እንዲሸጥለት የጠየቀውን ግለሰብ ‘ልሸጥልህ አልችልም’ ብሎ በመመለሱ ፖሊሶች ጠርቶ እንዳስያዘው እና በእጁ የድምጽ መለዋወጫ መሳሪያ (ወኪ ቶኪ) ይዞ በመገኘቱ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አባል ነህ በሚል ሰበብ መሆኑ ተገልጿል።

 

የፍዋዝ አባት አቶ ጁሀርና ቤተሰባቸው ብዛት ያላቸው ስደተኞችን ከተለያዩ ቦታዎች ስፖንሰር በማድረግ እንደሚታወቁና ልጃቸው እንዲፈታ የካናዳ መንግስት የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ ላለፉት ሁለት ሳምንታት በተደጋጋሚ ማሳወቃቸውን ለመረዳት ችለናል።

 

የትምህርት ጓደኞቹና የዊኒፔግ ክፍለ ግዛት ነዋሪዎች በድሬደዋ እስር ቤት የሚገኘው ፍዋዝ እንዲለቀቅ የካናዳ መንግስትን እየጠየቁ ሲሆን መንግስትም ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየተከታተለው ያለ ጉዳይ መሆኑን በውጭና አለም አቀፍ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በኩል አስታውቋል።

 

በትምህርት ቤትና በስራ ቦታው ምስጉን ነው የሚሉት ካናዳዊ ጓደኞቹ ፍዋዝ በአስቸኳይ እንዲለቀቅ ፊርም በማሰባሰብ ላይ መሆናቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ይጠቁማል።

 

በተመሳሳይ ሁኔታ የ42 አመቱ ካናዳዊ በሽር ማክታል ከሁለት አመት በላይ በኢትዮጵያ እስር ቤት እንደሚገኝ ይታወሳል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ