የጋዜጠኞችና የጋዜጦች ህልውና አደጋ ላይ ነው
የአንድ ጋዜጣ ዋጋ 7ብር ገብቷል
Ethiopia Zare (ሐሙስ ሚያዝያ 13 ቀን 2003 ዓ.ም April 21, 2011)፦ ሰሞኑን በጋዜጦችና በጽሔቶች ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ በርካታ ጋዜጦችንና ጋዜጠኞችን ከስራ ውጭ እንደሚያደርጋቸው እና የህትመት ስራ በአጠቃላይ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ መሆኑ ተገለጸ።
ማተሚያ ቤቶች የወረቀት ዋጋ መወደድን ምክንያት በማድረግ እስከ 45 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ ካደረጉበት ጊዜ አንስቶ በተለይ ብዙ ኮፒ ያሳትማሉ የሚባሉ ጋዜጦች በአንባቢ ላይ ያደረጉት ማስተካከያ ብዙ ሊያስገፋ እንደማይችል ከስፍራው የደረሰን ዘገባ ያስረዳል።
በአሁኑ ሰአት አንድ ጋዜጣ ቀደም ሲል ከነበረው እስከ አራት ገጽ መቀነስ የግድ ቢልም ዋጋውም ወደ ሰባት የኢትዮጵያ ብር ማሻቀቡ ካለው የኑሮ ውድነትን የገበያ ግሽበት አንጻር የአንባቢውን ቁጥር በእጅጉ እንደሚቀንሰው በተለይ ለኢትዮጵያ ዛሬ ቅርበት ያላቸው ጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የህትመት ዋጋው ከብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ጀምሮ በአሁኑ ሰአት ሌሎች ማተሚያ ቤቶችም ጭማሪውን ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።
በተያያዘም ሐበሻ ሪቪው በሚል መጠሪያ የህትመት ፈቃድ በማውጣት ስራውን አጠናቆ የሚገኘው አሳታሚ እስካሁን ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ማተሚያ ቤቶችና የፕሬስ መምሪያ ሀላፊዎች እግድ እንደጣሉበት የገለጸ ሲሆን በተለያየ ጊዜ እየተሸራረፈ የሚገኘው የፕሬስ ስራ ህልውናው ያከተመለት ነው ሲሉ አስተያየት ሰጭዎች ይተቻሉ።
የህትመት ዋጋን በተመለከተ የተቋቋመው የጋዜጠኞችና የአሳታሚዎች ግብር ሀይል ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ይነበባል።
“የጋዜጣና መጽሔት ሕትመት ዋጋ ጭማሪ ለፕሬስ ነጻነት አደጋ ነው” የጋዜጣና መጽሔት አሳታሚዎች አስተባባሪ ኮሚቴ
በሕገ መንግሥቱም ሆነ ሕገ መንግሥቱን መሠረት አድርገው በወጡ የፕሬስ ነፃነት ነክ ሕጎች ላይ መሠረት በማድረግ በርካታ ጋዜጦችና መጽሔቶች ተፈጥረዋል። ለኅብረተሰቡ መረጃ በመስጠትም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ። አማራጭ የሆነ መረጃ ለኅብረተሰቡ በመስጠት እየተጫወቱት ያለው ሚና በቀላሉ የሚገመት አይደለም። የገንዘብ አቅማቸው ደካማ በመሆኑ ሁሌም ህልውናቸው አደጋ ላይ ነው። ይህ ማለት እነሱም አማራጭ መረጃ የመስጠት ግዴታ፣ ሕዝብም አማራጭ መረጃ የማግኘት መብቱ ሁልጊዜ አደጋ ላይ ነው ማለት ነው።
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጋዜጣና የመጽሔቶች ማተሚያ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት የህልውናቸው ጥያቄ ወሳኝ ደረጃ ላይ ደርሷል። ማተሚያ ቤቶች የወረቀት ዋጋ ጨምሮብናል በሚል ምክንያት ዋጋ ላይ ጭማሪ ስላደረጉ ጋዜጣና መጽሔት አሳታሚዎች ሊሸከሙት የማይችል ደረጃ ላይ ደርሷል።
የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት 45 በመቶ የሚያክል ዋጋ ሲጨምር ሌሎች ማተሚያ ቤቶችም ተመሳሳይ ጭማሪ እያደረጉ ስለሆነ፣ በሁሉም ማተሚያ ቤቶች የሚታተሙ ጋዜጦችና መጽሔቶች ‹‹መኖር ወይም አለመኖር!›› የሚል ጥያቄ አንዣቦባቸዋል። በተለይ ደግሞ በግል ድርጅቶች ባለቤትነት ሥር ያሉ ጋዜጦችና መጽሔቶች ለተለያዩ ማተሚያ ቤቶች በዓመት ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ይከፍላሉ። የደንበኝነት ዕድሜያቸውም የአንዳንዶቹ ከ15 ዓመት በላይ ነው።
ካለው የጭማሪ መጠን ከፍተኛነት፣ ካለው የደንበኝነት ዕድሜ፣ ካሉት የደንበኞች ብዛትና ከሚከፈለው ገንዘብ መጠን ጋር ሲገናዘብ የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ከፍተኛውን ደረጃ ስለሚይዝ የጋዜጣና የመጽሔት አሳታሚዎች በጋራ ለብርሃንና ሰላም ደብዳቤ ጽፈው ነበር። በግልባጭም ለማተሚያ ድርጅቱ ቦርድና ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ኃላፊዎች ጽፈዋል። የአሳታሚዎች ጥያቄም በገንዘብ ዓይን ሲታይም ሆነ የሕዝብ አማራጭ መብት የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ስለሆነ ሁኔታውን ለማጥናትና አቋም ለመውሰድ የጭማሪው ተግባራዊነት ለሦስት ወራት ያህል እንዲቆይና ውይይቱ እንዲቀጥል የሚጠይቅ ነበር።
በዓለም ላይ የምርቶች ዋጋ እየጨመረ በመሄድ ላይ ስለሚገኝ በወረቀት ላይም ዋጋ ጨምሯል ቢባል አሳታሚዎች የምንጠብቀው ነው። የጭማሪው ዋጋ በእያንዳንዱ ጋዜጣና መጽሔት አሳታሚ ድርጅት ያሳደረገውን ጫና ግን ልንቀበለው ያስቸገረን መጠን ሆኗል።
ማተሚያ ቤቶች ሳይከስሩ፣ ጋዜጦችና መጽሔቶች ሳይዘጉ መኖርም መቀጠልም ይችላሉ ብለን እናምናለን። ለመፍትሔው በሁሉም በኩል ቅን የሆነ አመለካከት ካለ የጋዜጣና የመጽሔት አሳታሚዎች ስለ ዋጋ ጭማሪ እያሳሰበን ያለው ‹‹የዚህ ጋዜጣ ትርፍ ይቀንሳል፣ የዚህ መጽሔት ገቢ ይጓደላል ወይም ደግሞ ጋዜጦችና መጽሔቶች አቅም አጥተው ሕልውናቸውን ያጣሉ፤›› ከሚል መመዘኛ ብቻ አይደለም። ዋነኛው አሳሳቢ ጉዳይ በሕገ መንግሥቱና በሌሎች የሚዲያ ሕጎች ፕሬስ የተለያየ መረጃ የመስጠት መብትና ግዴታ አለበት፤ ሕዝብም መረጃ የማግኘት መብት አለው፤ ቢባልም ጋዜጦችና መጽሔቶች አቅም አጥተው ከተዘጉ በሕገ መንግሥቱ የተደነገገው መብት ተግባራዊ ሳይሆን ይቀራል። አማራጭ መረጃዎችና የተለያዩ አስተሳሰቦች በኅብረተሰቡ ውስጥ የማንሸራሸር ሁኔታ አይኖርም።
ስለሆነም የወረቀት ዋጋ ጨምሯል ተብሎ በጋዜጦችና በመጽሔቶች አሳታሚዎች ላይ የማይችሉት የዋጋ ጭማሪ መጫን የሚያስከትለው ችግር የአገር ችግር፣ መረጃ የማሠራጨትና የማግኘት ችግር እንደሚሆን በመገንዘብ ሕዝብም፣ መንግሥትም የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶችም ለችግሩ ልዩ ትኩረት ሰጥተው መፍትሔ ለማግኘት የበኩላቸውን እንዲወጡ እንጠይቃለን።



