አቶ ስዬ አብርሓ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጡ
[ሊያነቡት የሚገባ!]
“አውቃቸዋለሁ! በዚህች ሰዓት ከፍተኛ ስጋት ውስጥ ናቸው”
“90 በመቶ የሚሆኑት ጀኔራሎች ከትግራይ መሆናቸው ስህተት ነው”
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2003 ዓ.ም May 10, 2011)፦ የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር የአሁኑ የአንድነት ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ስዬ አብርሃ በሀገሪቱ ወቅታዊና ተጨባጭ ሁናቴዎች ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
አቶ ስዬ ካፒታል በመባል ለሚታወቀው የእንግሊዝኛ ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳብራሩት መቼም ይሁን መቼ ህዝብ በየትኛውም መንገድ የዲሞክራሲ ጥያቄ ማንሳቱ የማይቀር መሆኑንና ሀገሪቱ በአንድ ፓርቲ አገዛዝ ውስጥ ምንም አይነት ነጻ ተቋማት በሌሉበት ሁኔታ እንዳለች ገልጸዋል።
ለረዥም ዘመን አብረዋቸው ከታገሉት ከእነ አቶ ገብሩ አስራት አረና ትግራይ ይልቅ እንዴት ህብረ ብሔራዊ በሆነው በአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ እንደታቀፉ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፦ “ይህ ሊያስደንቅ አይገባም። እኔና ገብሩ ህወሀት ውስጥ አብረን ነበርን ማለት ለዘላለሙ በአንድ ፓርቲ ውስጥ ታቅፈን እንኖራለን ማለት አይደለም። በበኩሌ እንደ ህወሀት ካለ በብሄር የተዋቀረ ድርጅት ውስጥ የፖለቲካ ትግሌን ማካሄድ አስፈላጊ ነው ብዬ ያመንኩበት ዘመን ነበር። አሁን ደግሞ ወቅቱ የሚጠይቀው የተለያዩ የአገሪቱ ብሄሮች በአንድ ጥላ ስር ታቅፈው በአንድነት ዲሞክራሲያዊ ትግል የሚያደርጉበት ጊዜ ነው የሚል እምነት አለኝ። ለዚህም ነው የአንድነት ፓርቲን የተቀላቀልኩት።” ብለዋል። አያይዘውም ያ ማለት ግን በብሄር ወይንም በጎሳ በተዋቀሩ ፓርቲዎች ስር ታቅፈው የሚታገሉ ዜጎች በህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎች ስር ከታቀፉት ዜጎች ያነሰ ወይም የላቀ ኢትዮጵያዊ ናቸው ማለት ያለመሆኑን አስምረውበታል።
አቶ ስዬ በቃለ ምልልሱ ፓርቲያቸው አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ለመጭው አምስት አመት ፕሮግራም መዘርጋቱን የገለጹ ሲሆን በሀገሪቱ የዲሞክራሲ ስርአት ተዘርግቶ ሁሉም ዜጋ ሀሳቡን በነጻነት የሚገልጽበትና በድምጹ መሪዎቹን የሚመርጥበት ነጸ ዘመን እንዲመጣ የሚታገሉበትን ስልት መንደፋቸውን ጠቁመዋል።
“አሁን ያለነው ነጻ ተቋማት የሌሉበትና የአንድ ፓርቲ አመራር የነገሰበት ስርአት ውስጥ ነው” የሚሉት አቶ ስዬ “ገዥው ፓርቲ ሁሉን ነገር የሚቆጣጠርበትና ነጻ የህግ ተቋማት የሌሉበት፤ ጦሩም ሆነ የደህንነት ተቋማቱ በነጻነት ይሰራሉ ማለት በማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ ነን። ይህ ግን መቆም አለበት። እነዚህ ሁኔታዎች ካልተስተካከሉ አብላጫ የህዝብ ድምጽ ማግኘት ብቻውን ወደ ሽግግር ያመራል የሚል ዋስትና አያስገኝም” ሲሉ ተሟግተዋል።
በመካከለኛው ምስራቅና በሰሜን አፍሪካ እየተስተዋለ ያለው ህዝባዊ እንቅስቃሴ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ አይቀሬ ነው በሚል ፓርቲያቸው ምልከታውን ቢያቀርብም ኢህአዴግ ግን ህዝቡ የኢኮኖሚ እድገት የሚያጣጥምበት ወቅት ላይ በመሆኑ ይህ በኛ ሀገር አይታሰብም ማለቱን እንዴት ያዩታል የሚል ጥያቄም ቀርቦላቸው ነበር። “ሌላ ምን ሊሉ ኖሯል?!” ይላሉ አቶ ስዬ “ሁሉም አንባገነኖች ቢሆኑ ስለራሳቸው ውድቀት ማውራት አይፈልጉም። ሙባረክም ይህንኑ ነው ያደረጉት። ግብጽ ቱኒዚያ አይደለችም ሲሉን ነበር። አሁን ደግሞ ጋዳፊ ሊብያ ግምጽ አይደለችም እያሉ ነው።
“ስለሰዎቹ (ኢህአዴግ) ካለኝ እውቀት ተነስቸ በዚህች ሰአት ከፍተኛ ሰጋት ውስጥ ስለመሆናቸው መናገር እችላለሁ። ሰላማዊው ህዝባዊ ቁጣ እኛ ጋር ቢመጣ በሚል ማክሸፍ የሚችሉበትን ማናቸውንም አይነት ሴራና እኩይ እቅዶች በመንደፍ ላይ ነው ሊገኙ የሚችሉት። በአደባባይ ግን ይህ በኛ አገር አይታሰብም ይላሉ። ”የመከላከያ ሰራዊቱን በተመለከተም ሊኖረው ስለሚችለው ሚና ሲያብራሩ ጦሩ ከማን ጋር ይወግናል ከማለታችን በፊት ሁለት ወሳኝ ተግባራት መሟላት አለባቸው ባይ ናቸው። እንደ አቶ ስዬ እምነት ፍርሀቱን አስወግዶ ለለውጥ የሚንቀሳቀሰው ህዝባዊ ሰልፈኛ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር መሆን ይጠበቅበታል። በግብጽና ቱኒዚያም ሆነው እንደዚያ ነው። ከሁሉ በላይ ወሳኙ ነገር ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ፍርሀቱን አስወግዶ መውጣቱ እና በጽናት መቆሙ ላይ ነው።
“ቀጣዩ ወሳኝ ተግባር ደግሞ ተቃውሞው ወደ ኃይል እንዲለወጥ መንግስት የሚዘረጋቸውን ወጥመዶች ሁሉ ነቅቶ በመጠበቅ በሰላማዊነቱ ላይ ጸንቶ መቆየቱ ነው” ይላሉ የቀድሞው መከላከያ ሚኒስተር አቶ ስዬ። ለዚህ ደግሞ የግብጽ ሰልፈኞችን አይነታ ምሳሌ አድርገው ይጠቅሷቸዋል። “ጦሩን በተመለከተ የሚወስዱት አቋም እኛ ለእነሱ በሚኖረን አተያይና አቀራረብ ይወሰናል። የሚሉት አቶ ስዬ አመለካከታችንን ማስተካከል ይገባናል ሲሉ እንደሚከተለው አብራርተዋል።
“አብዛኞቹ ጀኔራሎች ቀድሞ የህወሀት አባላት የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ናቸው። እንደኛው ኢትዮጵያዊያን ናቸውና ልናቅፋቸው ይገባል። የምንነጥላቸው ከሆነ ግን የገዥዎቹ መጠቀሚያ ነው የሚሆኑት። ቢያንስ ቢያንስ በዚህች ሀገር ነጻነት ለማምጣት ብለው ደርግን የታገሉ፣ በኤርትራ ጦርነትም ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉ ናቸው። ያንን ዋጋ ሰጥተን ልናቅፋቸው ነው የሚገባው።
“እርግጥ ነው በአሁኑ ወቅት 90 በመቶ ሚሆኑት ጄኔራሎች የትግራይ ተወላጆች ናቸው። ይህ ፍጹም ተገቢ አይደለም። መቀየርም ያለበት ጉዳይ ነው ይሁንና ይህ የተሿሚዎቹ ጥፋት ላይሆን ይችላል። በማናቸውም መስፈርት ደግሞ ኢትዮጵያዊነታቸውን ሊያሳጣቸው አይችልም። መለስ የትግራይ ሰው ናቸው ማለት ሁሉም ትግሬ የመለስ ደጋፊ ነው ማለት አይደለም። ሁላችንም ኢትዮጵያዊያን ነን። በአንድ ላይ የሚያቆመንም ተስፋ ነው። የዚህች አገር የጋራ ባለቤቶችና እድገቷን አላሚዎች ነን። መቆም ያለብን በህብረት ነው።
አቶ ስዬ አብርሃ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሰጡትን ቃለ ምልልስ ለማንበብ ይህንን ይጫኑ!



