በስደት ከሚገኙ የቀድሞ የኢሠማ መሪዎች የተሰጠ መግለጫ
Ethiopia Zare (ኀሙስ ሚያዝያ 23 ቀን 2000 ዓ.ም. May 1, 2008)፦ ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን ዓለም የሠርቶ አደሮች ቀንን ምክንያት በማድረግ በስደት የሚገኙ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት መሪዎች "የወያኔን ድቅድቅ ጨለማ ላብ አደሩ በትግል ችቦ ያበራዋል!" በሚል ርዕስ ባለ ሁለት ገጽ መግለጫ አወጡ።
በመግለጫቸው "... ወያኔ የዴሞክራሲ መሠረት የሆኑትን የሲቪክ ማኅበራት ... እያፈራረሰ እና እየናደ "ዴሞክራሲን እየገነባሁ ነው" የሚለውን ቧልት ቀጥሎበታል። በሀገራችን ነፃ የሲቪክ ማኅበራት ያሉበት ሁኔታ የወያኔን ፀረ-ዴሞክራሲያዊነትና አፋኝነት ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ..." ሲሉ ገዥውን ፓርቲ ኮንነዋል።
"የወያኔን አምባገነናዊ እና ፋሽስታዊ አገዛዝ ለማንበርከክ እና የህዝባችንን ነፃነት ለማረጋገጥ በሚካሄድ ህዝባዊ ትግል ተሰባስበን በጋራ እንድንታገል ለኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበራት የዓለም ሠርቶ አደሮች የትግል አጋርነት ቀን በሆነው ሜይ ዴይ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ..." ሲሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።
አክለውም በመግለጫቸው "... የኢትዮጵያ ህዝብ በአምባገነናዊ እና ፋሽስታዊ እመቃ ስር እየተረገጠ እና እየተጨፈጨፈ ለሠራተኛው ህዝብ የዴሞክራሲ ደሴት መገንባት አይቻልም። በመሆኑም ወያኔ በህዝባችን ላይ የጫነውን ድቅድቅ ጨለማ በትግል ችቦ ለማብራት ሠራተኛው ህዝብ በግንቦቱ 1997 ምርጫ እንዳደረገው ሁሉ ዛሬም ክንዱን ከፀረ-ወያኔ ታጋይ ኃይሎች ጋር ማንሳትና ከጎናቸው ቆሞ ሁለንተናዊ ድጋፍ መስጠትና በትግሉ ሙሉ በሙሉ መሳተፍ የነፃነት ብቸኛው መንገድ መሆኑን አምኖ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል። ..." በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል። (ሙሉውን መግለጫ አስነብበኝ)



